“ከዛሬዋ ጨረቃ መውጣት ጋር ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥና በመላው ዓለም ራማዳንን የምታከብሩ ሙስሊሞች ሁሉ ሰላምታዬና መልካም ምኞቴ ይድረሣችሁ” ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ዛሬ መልዕክት አውጥተዋል።
ቅዱስ ቁርዓን ለነብዩ መሃመድ በፍቅርና በፀሎት የተገለፀበትን ቅዱሱን ራማዳን ወር ሙስሊሞች እንደሚያስቡት በመልዕክታቸው ጠቅሰው ይህንን ቅዱስ ጊዜ ብዙዎች የሚያከብሩት በፆም፣ በዘካ፣ በሶላትና ቅዱስ ቁርዓንን በመቅራት እንደሆነ አስታውሰዋል።
“ራማዳን መንፈሣዊ ብልፅግናን ለማጥለቅና አምላክ የቸረንን የበዙ በረከቶች ማድነቃችንን ለማደስም እራሳችንን የምንመረምርበት ጊዜ ነው” ብለዋል ፕሬዚዳንት ትረምፕ።
ፕሬዚዳንቱ መልዕክታቸውን በመቀጠልም “በዚህ የምሥጋናና የፅሞና መንፈስ ራማዳንን የሚያከብሩ ማኅበረሰቦቻችንን ሊጠናክሩ፣ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሊረዱ፣ ቅዱስ ሕይወትን እንደምን አድርገን እንደምንመራም ለሌሎች መልካም አርአያ ሊሆኑ ይችላሉ” ብለዋል።
“ራማዳን፤ ሙስሊሞች በአሜሪካዊው ሕይወት ገፅታ ላይ የሚያኖሩትን የሐይማኖታዊ ጥልፍ ካብታምነት ያስታውሰናል” የሚለው የፕሬዚዳንቱ የዛሬው መልዕክት “ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሐይማኖት ነፃነትን በሚያጠናክርና ሐይማኖታዊ ሥርዓትን በሚያከብር ሕገመንግሥት ሥር እንኖር ዘንድ ሁላችንም ታድለናል” ሲል ይቀጥላል።
ሙስሊሞች ራማዳንን በሕሊናቸው መመራትና ያለመንግሥት ጣልቃገብነት ማክበር እንደሚችሉ ሕገመንግሥቱ እንደሚያረጋግጥ የፕሬዚዳንት ትረምፕ መልዕክት ያስታውስና በዚህም አሜሪካዊያን ሁሉ የሰብዕናን ነፍስያ በጥልቀት መረዳታቸውን እንዲያበዙም ሕገመንግሥቱ የተለያዩ ዕድሎችን ያመቻቸ መሆኑን አስገንዝበዋል።
“ብዙ ሰዎች ራማዳንን ለማክበር በአንድ እንደቆሙ ሁሉ ሜላንያና እኔም ለዚህ የተባረከ ወር በተስፋ እንቀላቀላለን። ራማዳን ሙባረክ” ብለዋል የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ቅዱስ ራማዳንን ምክንያት በማድረግ ዛሬ ባወጡት በዚህ መልዕክታቸው።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ