ትረምፕ ዛሬ በትዊተራቸው “ኢራን በጣም ከባድ ስህተት ሰራች” ብለዋል። ባለፈው ሳምንት ሆርሙዝ ሰርጥ ላይ በሁለት የነዳጅ መርከቦች ላይ “ደረሰ” ከተባለው ጥቃት በኋላ በዋሺንግተንና በቴህራን መካከል ውጥረቱ መጋጋሉን ቀጥሏል።
ዛሬ ቀደም ሲል የኢራን አብዮታዊ ዘብ አየር ክልላችን የገባ የዩናይትድ ስቴትስ /RQ-4 GLLOBAL HAWK/ የተባለ ድሮን መትተን ጥለናል ሲል አስታውቀዋል።
“ለኛ ድንበሮቻችን ቀይ መስመር ናቸው፤ ድንበራችንን ጥሶ የተገኘ ጠላት ይደመሰሳል” ሲሉ የኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዥ ጄኔራል ሁሴን ሳላሚ ተናግረዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎችን የመካከለኛው ምሥራቅ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው የዩናያትድ ስቴትስ ማዕከላዊ ዕዝ ኢራን ያለችውን ወዲያውኑ ውድቅ አድርጓል።
በዓለምቀፍ የአየር ክልል ላይ በነበረ ዩናይት ስቴትስ የቅኝት ንብረት ላይ ያለምንም ትንኮሳ የተካሄደ ጥቃት ነው ያሉት የሴንትኮም ቃል አቀባይ ሻምበል ቢል አርባን በመግለጫቸው አውሮፕላኑ ትናንት በሆርሙዝ ሰርጥ በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለ ከየብስ በተተኮሰ ሚሳይል ተመትቶ መጣሉን አስረድተዋል።
222 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣው ድሮኑ በቀን መቶ ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው አካባቢ መቃኘት የሚችል እንደነበር ተገልጿል። ዩናይትድ ስቴትስ ስብርባሪውን የሚሰበስብ ቡድን ወደአካባቢው እንደምትልክ ገልፃለች።
የዩናይትስ ስቴትስ መፋጠጥ ስጋት የደቡብ ካሮላይናው ሪፖብሊካን ሴነተር ሊንዚ ግራም ከፕሬዚዳንት ትረምፕ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በሰጡት ቃል መጥፎ ደረጃ ላይ እየደረስን ነው ያሉንን አማራጮች ሁሉ አሟጠናል የሚል ዕምነት ላይ ደርሰዋል ብለዋል።
የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ በበኩላቸው አደገኛ ሁኔታ ነው፤ ዩናይትድ ስቴትስ ከኢራን ጋር ጦርነት ውስጥ የመግባት ፍላጎት የላትም ብለዋል።
አያይዘውም ውጥረቱ ተጋግሏል። ጠንካሮች ሆነን ስትራተጂያዊ በሆነ መንገድ ጥቅሞቻችንን ማስከበር ይኖርብናል ሲሉ ተደምጠዋል።
የሩስያ ፕሬዚዳንት ቪላዲሚር ፑቲን ዩናይትድ ስቴትስ ለድሮኑ ተመትቶ መውደቅ የበቀል ዕርምጃ ከመውሰድ እንድትቆጠብ አስጠንቅቀዋል፡፡ ኃይል የተጠቀመች እንደሆን በክልሉ ከባድ ጥፋት ያስከትላል ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ