በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ከአል ቡርሃን ጋራ መሥራትን እንደሚመርጡ አስታወቁ


ኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያይስ አፈወርቂ
ኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያይስ አፈወርቂ

በሱዳን እየተፋለሙ ያሉ የጦር ጀነራሎች፣ በወኪሎቻቸው በኩል ለመደራደር ተስማምተዋል እየተባለ ውጊያው ግን በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት፤ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያይስ አፈወርቂ፣ መንግሥታቸው፥ ከሱዳን ጦር ጠቅላይ አዛዥ ጀነራል አብዱል ፈታሕ አልቡርሃን ጋራ መሥራትን እንደሚመርጥ አስታውቀዋል።

የቀድሞ የሱዳን ፕሬዚዳንት አልበሽር፣ እ.አ.አ. በ2019 በሕዝብ ተቃውሞ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ፣ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ፣ “ከሕዝብ ጋር የመወገን ሥራ ሠርቷል” ያሉትን በጀነራል አል ቡርሃን የሚመራውን ሠራዊት አድንቀዋል።

ላለፉት አራት ዓመታት፣ ኤርትራ ከሱዳን ጋራ አዎንታዊ በኾነ የሁለትዮሽ ግንኙነት መቆየትዋን ያወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ሱዳንን ለተፈላጊው ሽግግር የማብቃቱን ሓላፊነት መወጣት የሚችሉት፣ ጀነራል አል ቡርሃን እንደኾኑ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች፣ በተደጋጋሚ ያደረጉት የተኩስ ማቆም ስምምነት ሳይሳካ ቀርቶ ውጊያው ቀጥሏል። በሁለቱ ጀነራሎች የሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት የሚካሔደው ትጥቃዊ ፍልሚያ፣ በመቶዎች የሚቆጥሩ ሰዎችን ለኅልፈት ዳርጓል፤ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን፣ አገራቸውን ለቅቀው ለመሰደድ መጣደፋቸውን ቀጥለዋል።

ጎረቤት ሱዳን በዚኽ ጸጥታዊ ቀውስ ውስጥ በተዘፈቀችበት ኹኔታ፣ በትላንትናው ዕለት መግለጫ የሰጡት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈ ወርቂ፣ ለሱዳን መታወክ ጥንስስ የኾነው ትልቁ ስሕተት የተፈጸመው፣ በፕሬዚዳንት ኣልበሽር አገዛዝ ወቅት ነበር ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። “ሱዳናውያን እንደ አገር አንድ የመኾን ዕድላቸው አመዝኖ ሳለ፣ ደቡብ ሱዳን እንድትገነጠል መፍቀዳቸው፣ የአገሪቱ ቀንደኛ እና ታሪካዊ ስሕተት ነበር፤” ሲሉ አብራርተዋል።

ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ፣ በቃለ ምልልሱ ወቅት ያነሡት ሌላው ጉዳይ፣ ከሱዳን በመውጣት ላይ የሚገኙ ስደተኞችን አስመልክተው የተናገሩት ነው፡፡ ኤርትራ እንደ ጎረቤቶቿ ሀገራት ሁሉ፣ ስደተኞችን በመቀበል እና ወደ ሦስተኛ አገር በማሻገር የድርሻዋን ስትፈጽም መቆየትዋን ጠቅሰዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም፣ አሁንም ፖሊሲያችን፥ እንደ ዐቅማችን ተፈናቃዮችን ለመቀበል በራችንን ክፍት ማድረግ ነው፤ ብለዋል፡፡ ይኹንና፣ ተሰድደው ወደ ኤርትራ ለገቡ ችግረኞች መንግሥታቸው በሚከተለው መረዳጃ፣ “የሚዘረጋ የርዳታ ድንኳን የለም፤” ሲሉ፣ የስደተኞች ካምፕ የመክፈት ዕቅድ እንደሌላቸው አስታውቀዋል።

“አንድ እና የተዋሐደ ሠራዊት የመገንባት እና የሥልጣን ክፍፍል” የሚል አጀንዳ፣የሱዳን ግጭት ዋና ምክንያት እንደኾነ የሚጠቅሱት ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ፣ “እርባና የሌለው ምክንያት ነው” ሲሉ ተችተዋል፡፡ የጎረቤት አገሮች እና ሌሎች ኀይሎች ችግሩን ለመፍታት በሚል የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት፣ አጋዥ ወይም ማሟያ እንጂ የኹነኛው መፍትሔ ተኪ ሊኾን እንደማይችል አሳስበዋል፡፡ ይልቁንም፣ እንደ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አገላለጽ፣ የሱዳን ሕዝብ የራሱን ጉዳይ ራሱ ለመፍታት ዕድል እንዲሰጠው ጥሪ አቅርበዋል።

ሦስት ሳምንታት ያለፉት የሱዳኑ ትጥቃዊ ግጭት፣ ከ500 በላይ ሰዎች ለኅልፈት ሲዳረጉ፣ በ10ሺሕዎች የሚቆጠሩቱ ደግሞ መፈናቀላቸው እየተገለጸ ይገኛል፡፡

XS
SM
MD
LG