በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን የፆታ ሁከት ተጠያቂነት ትዕዛዝ ፈረሙ


ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

ከግጭት ጋር የተያያዘ ፆታ ተኮር ጥቃትን ለመዋጋት ዩናይትድ ስቴትስ የምታደርገውን ጥረት ለማጠናከር የተባለ የተጠያቂነት ትዕዛዝ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ፈርመዋል።

ባይደን ትናንት ያወጡት ይህ ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዛቸው ትኩረት ሳይሰጣቸው፣ ወይም ሳይዘገቡ ወይም ተዘንግተው የሚያልፉ የወንጀል አድራጎቶች በተጠያቂነት እንዲያስይዙ ለማድረግ የታሰበ እንደሆነ ተገልጿል።

ፕሬዚዳንቱ ትዕዛዙን ከመፈረማቸው ቀደም ሲል ዋይት ሀውስ ዌብሳይቱ ላይ ባሰፈረው መግለጫ “ዩናይትድ ስቴትስ በግጭት ጊዜ የሚደርሱ ወሲባዊ ጥቃቶችን ... አጋጣሚዎች ብቻ አድርጋ አትቀበልም” ብሏል።

ወደፊት ሊሞከሩ የሚችሉ ጥቃቶችን ለመከላከል የህግ፣ የፖሊሲ፣ የዲፕሎማሲና የፋይናንስ አቅሞችን ጨምሮ ሁሉንም እምርጃዎች በመጠቀም ሰለባዎቹን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗንም መግለጫው አስታውቋል።

ፕሬዚዳንቱ ይህን ትዕዛዝ ያወጡት በግጭቶች ውስጥ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል እንግሊዝ እያስተናገደች ባለችው ዓለምአቀፍ የሚኒስትሮች ስብሰባ ወቅት መሆኑን ዋይት ሃውስ አስታውሶ “መሰል ጥቃቶች የዩክሬንን ግዛት በያዘችው ሩሲያና ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም እየተፈፀመ በሚገኝበት ወቅት ነው” ብሏል።

የዛሬው እምርጃ የፆታ ፍትኅና እኩልነትን ማረጋገጥን፣ የግጭት መሠረታዊ መንስዔዎች መፍትኄ መሻትን፣ የሴቶችን የሰላምና ደኅንነት ጨምሮ በግጭቶች ውስጥ የሚፈፀሙ ፆታ ተኮር ሁከቶችን ለመከላከል አስተዳደሩ የሚያደርገውን ሁሉን አቀፍ ጥረት የሚደግፍ መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል።

ከግጭቶች ጋር በተያያዘ ለሚፈፀም እያንዳንዱ የመድፈር አድራጎት ከ10 እስከ 20 የሚደርሱ ሪፖርት ሳይደረጉ እንደሚቀሩ መግለፁን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።

በዚህ ወር የወጣው የመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርት የሩሲያ ወታደሮች በዩክሬን ሲቪሎች ላይ መድፈርን ጨምሮ ሌሎች የጦር ወንጀሎችን ፈፅመዋል ማለቱን ኤቢሲ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

የፕሬዚዳንት ባይደን ትዕዛዝ ከግጭቶች ጋር በተያያዘ ወሲባዊ ሁከት ተጠያቂ በሚሆኑ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ የገንዘብ ሚኒስቴርና ሌሎችም የፌደራሉ መንግሥት ተቋማት ተጨማሪ እርምጃዎችን እንዲወስዱ መመሪያ መስጠቱ ታውቋል።

XS
SM
MD
LG