የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዳላስ-ቴክሳስ ተገኝተው በሰሞኑ ግድያ ጉዳት ለደረሰባቸው የፖሊስ መኮንኖች ቤተሰቦች፣ ለባልደረቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው እንዲሁም ለአሜሪካዊያን ሁሉ “ሁላችንም አንድ አሜሪካዊ ቤተሰብ ነን” ሲሉ የአንድነትና የማፅናኛ ንግግር አድርገዋል፡፡
ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ትብብር ድርጅቱ - ኔቶ ስብሰባ ላይ ፈጥነው ወደ ሃገራቸው የተመለሱት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዜጎቻቸው ተስፋ መቁረጥን እንዲጠየፉ ጠይቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ “ለተመልካች የምንመስለውን ያህል የተለያየን፤ የተራራቅን አይደለንም” ብለዋል፡፡
ሰሞኑን የፖሊስ አባላት በጥቁር አሜሪካዊያን ላይ የተፈፀሙ ግድያዎችን፤ ዳላስ ውስጥ በአንድ ጥቁር ጥይት የተገደሉ አምስት የፖሊስ አባላትን አስታውሰዋል፡፡
እጅግ የበዙ የአሜሪካ ፖሊስ አባላት ተግባራቸውን በአግባቡ የሚወጡና ክብር የሚገባቸው መሆናቸውን ያመለከቱት ፕሬዚዳንት ኦባማ የወደቁትን መኮንኖች በስም እየጠሩ ዘክረዋቸዋል፡፡
የሁሉም ሃይማኖቶች መሪዎች፣ የሟቾች ቤተሰቦችና ወዳጆች፣ እንደራሴዎች፣ ቀዳሚት ዕመቤት ሚሼል ኦባማ፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽና ባለቤታቸው ላውራ ቡሽ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንና ባለቤታቸው ዶ/ር ጂል ባይደን ተገኝተዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽም ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር ተመሣሣይ የአንድነት መልዕክት ያለው ንግግር አድርገዋል፡፡
ትናንት ምሽት ላይ ከሺህ በላይ የሚሆኑ አሜሪካዊያን ዘር ሳይለዩ ለወደቁት ሁሉ ሻማ አብርተው አስበዋቸዋል፡፡
ለተጨማሪ የተያያዙትን የድምፅ ፋይሎች ያዳምጡ፡፡