በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኅዳሴ ጉዳይ የትረምፕ ንግግርና ምላሾች


ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ከሱዳንና ከእሥራኤል መሪዎች ጋር በስልክ ሲነጋገሩ /ከስክሪን የተወሰደ፤ ዓርብ፣ ጥቅምት 13/2013 ዓ.ም./
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ከሱዳንና ከእሥራኤል መሪዎች ጋር በስልክ ሲነጋገሩ /ከስክሪን የተወሰደ፤ ዓርብ፣ ጥቅምት 13/2013 ዓ.ም./

ግብፅ ታላቁ ኅዳሴ ግድብን እንድታፈርስ መምከራቸውንና እርምጃውን እንደሚያበረታቱም የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ መናገራቸውን ተከትሎ ከተለያዩ አካባቢዎች የተቃውሞ ድምፆች እየተሰሙ ነው።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ትናንት ባወጣው መግለጫ “ኢትዮጵያ በፈጣሪዋ ታምና በህዝቧ አንድነትና ፅናት የቆመች ሃገር ናት፤ ጥቂት ሰጥተው ብዙ ሊያዝዟት በሚሞክሩ ተማምና አታውቅም፤ ህይወታቸውን ሰጥተው ሊያዘዟት በተዘጋጁ ልጆቿ እንጂ...” ብሏል።

መግለጫው አክሎም “ኅዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ግድብ ነው፤ ኢትዮጵያዊያን አሰቡት፣ ኢትዮጵያዊያን ጀመሩት፣ ኢትዮጵያዊያን ገነቡት፣ ኢትዮጵያዊያን ይጨርሱታል፤ አይቀሬ ነው” ብሏል።

ኢትዮጵያዊያን በአንድነት እንዲቆሙ የተጣራው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት መግለጫ “በምንምና በማንም ካሰብነው መንገድ አንቀርም፤ ሁላችንም በየቦታችን ሃያ አራት ሰዓት ለኢትዮጵያ እንቁም” ብሏል።

በሌላ በኩል ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ከሱዳንና ከእሥራኤል መሪዎች ጋር በስልክ በተነጋገሩበት ወቅት ኅዳሴ ግድብን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት ላይ አዲስ አበባ የሚገኙት በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ማይክ ራይነር ማብራሪያ እንዲሰጧቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ትናንት ቢሯቸው ጠርተው ያነጋገሯቸው መሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።

ግድቡን በተመለከተ “በፕሬዚዳንቱ የተሰጠው አስተያየት አሳሳች” መሆኑን አቶ ገዱ አመልክተው “የአባይን ውኃ ፍሰት እንደማያቆም” ተናግረዋል።

“በተቀማጭ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ጦርነትን ማነሳሳት አንድም የሁለቱን ሃገሮች /የኢትዮጵያንና የዩናይትድ ስቴትስን/ የኖረና ስትራተጂካዊ ግንኙነት አያንፀባርቅም፤ አንድም ሃገሮች ግንኙነቶች የሚገዙበትን ዓለምአቀፍ ህግ የሚፃረር ነው” ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም “ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ ላይ ለሚሠነዘሩ ዛቻዎች ጨርሶ እንደማትንበረከክና በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ መሠረት በሦስቱ ሃገሮች መካከል እየተካሄደ ባለው ድርድር ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን” ለአሜሪካው አምባሳደር ያረጋገጡላቸው መሆኑን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መረጃ አመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ተጠሪ የሆኑት ዮሴፕ ቦሬል ትናንት ባወጡት መግለጫ በአባይ ተፋሰስ ውስጥ የሚኖሩ ከሁለት መቶ ሃምሣ ሚሊየን በላይ ሰዎች በኅዳሴ ግድብ አሞላል ላይ “በድርድር ይደረስበታል” ተብሎ እየተጠበቀ ካለው ስምምነት ተጠቃሚ ለመሆን ዝግጁ መሆናቸውንና በውኃ ደኅንነት፣ በመስኖ፣ በግብርና ምርትና የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት እየጠበቁ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በውኃ አሞላሉ ላይ “ስምምነት ላይ ይደርሳሉ” ተብሎ እየተጠበቀ መሆኑን ሚስተር ቦሬል ጠቁመው “ይህ ጊዜ ውጥረትን ለማባባስ ሳይሆን ለተግባር የተመቸ ነው” ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ተግባር አገልግሎት በዌብ ሳይቱ ላይ ትናንት ባወጣው የኅብረቱ ከፍተኛ ተጠሪ ዮሴፕ ቦሬል መግለጫ የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር በሆነችው በደቡብ አፍሪካ የተያዘውን ጥረት የአውሮፓ ኅብረት ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፍ አመልክተው ድርድሮቹ እንደገና ተጀምረው በተሣካ ሁኔታ እንዲጠናቀቁ ኅብረቱ እንደሚጠብቅ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ በቀጥታ በፃፉት ደብዳቤ “ፀብ የማነሳሳት አድራጎትዎ በእናት ሃገሬ ላይ የእጅ አዙር ጦርነት የማወጅን ያህል ነው” ሲሉ ተቃውሟቸውን በብርቱ ቃላት ያሰሙት የኔቫዳ ግዛት ምክር ቤት አባል አሌግዛንደር አሰፋ ፕሬዚዳንቱ አቋማቸውን በድጋሚ እንዲመረምሩ ጠይቀዋል።

የኔቫዳ ግዛት ምክር ቤት አባል አሌግዛንደር አሰፋ በኅዳሴ ጉዳይ ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የላኩት ደብዳቤ
የኔቫዳ ግዛት ምክር ቤት አባል አሌግዛንደር አሰፋ በኅዳሴ ጉዳይ ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የላኩት ደብዳቤ

ዩናይትድ ስቴትስ ሁሉንም ሃገሮች በእኩልነት እንድትመለከትና ሃገሮቹን ወደ ኅብረት ማምጣት ላይ እንደታተኩር እንደራሴው አሳበዋል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ በኅዳሴ ጉዳይ - ከምላሾች ጋር
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:58 0:00



XS
SM
MD
LG