በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በቱርክና ሶሪያው ርዕደ መሬት ከ1ሺ500 በላይ ሰዎች ሞቱ


በቱርክና ሶሪያው ርዕደ መሬት ከ1ሺ500 በላይ ሰዎች ሞቱ
በቱርክና ሶሪያው ርዕደ መሬት ከ1ሺ500 በላይ ሰዎች ሞቱ

በቱርክ እና ሶሪያ ወሰን አቅራቢያ ጋዜንቴፕ በተባለው ስፍራ ዛሬ ሰኞ የደረሰው ከባድ ርዕደ መሬት ከ1ሺ 500 በላይ ሰዎችን መግደሉ ተነገረ፡፡

በሬክተል ስኬል 7.5 መሆኑ ከተነገረለት የርዕደ መሬት ከወዳደቁ የህንጻ ፍርስራሾች ስር በህይወት የተረፉ ሰዎችን የማፈላለግ ስራ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የቱርክ ፕሬዚዳንት ጣይብ ኤርዶዋን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ቱርክ ቢያንስ 912 ሰዎች የሞቱባት ሲሆን 5ሺ400 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ተናግረዋል፡፡ 2ሺ800 የሚሆኑ ህንጻዎች መውደቃቸውንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

ኤርዶዋን ጣይብ በመግለጫቸው “ርዕደ መሬቱ በደረሰበት ክልል ውስጥ የሚገኙ የወዳደቁ ህንጻዎችን የማጽዳቱ ሥራ የቀጠለ ሲሆን፣ በአደጋው የሞቱትና የቆሰሉት ሰዎች ቁጥር ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነና በምን ያህል ሊጨምር እንደሚችል አላወቅንም” ብለዋል፡፡

የሶሪያ የጤና ባለሥልጣናት በበኩላቸው በመንግሥት ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች ቢያንስ 371 ሰዎች በአደጋው መሞታቸው ሲገልጹ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ደግሞ አማጽያኑ በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች በትንሹ 221 ሰዎች መሞታቸውን ገልጸዋል፡፡

ርዕደ መሬቱ የጋዜንቴፕ ታሪካዊ ቤተ እምነትንና በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች ታሪካዊ ህንጻዎችን ማውደሙ ተነግሯል፡፡

የቱርክ ከተማ በሆነችው መርሲን ውስጥ ነዋሪ የሆኑት ኑርሃን ኪራል ለቪኦኤ የቱሪክ አገልግሎት እንደተናገሩት ርዕደ መሬቱ ለአንድ ደቂቃ ያህል ጊዜ ቆይቷል፡፡

ኪራል በአደጋው ጊዜ የነበሩበትን ሁኔታ ሲገልጹ “የርዕደ መሬቱ ከእንቅልፋችን እንደቀሰቀሰን ወዲያውኑ ከመኝታችን ተነሳን፡፡ የህንጻው ፍርስራሽ ከጭስ መውጫው በኩል ወደቀ፡፡ በህንጻው መካከል ካሉ ባዶ ስፍራዎችም ፍርስራሾች መወዳደቅ ጀመሩ፡፡ እጅግ በጣም አስፈሪ ነበር” ብለዋል፡፡

የሶሪያ አሜሪካውያን ህክምና ማህበረሰብ በሶሪያ ያሉት ሆስፒታሎች ሞልተው በሽተኞች በየኮሪደሩ መተላለፊያዎች ተጨናንቀው እንደሚታዩ ገልጿል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ከከቡልጋሪያ፣ ክሮሽያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ፈረንሳይ፣ ግሪክ፣ ሃንጋሪ፣ ማልታ ኔዘርላንድ፣ ፖላንድ እና ሮማኒያ የተወጣጡ የአደጋ ጊዜ እርዳታ ሰጭዎችን ወደ ሥፍራው መላኩን ገልጿል፡፡

ሩሲያም የነፍስ አድን ቡድን ሰራተኞችን በአደጋው ወደ ተጎዱ ቱርክ እና ሶሪያ ለመላክ እየተዘጋጀች መሆኑን አስታውቃለች፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን ፕሬዚዳንት ባይደን የአገሪቱን የዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲን እና ሌሎች የፌዴራል አጋሮች በአደጋው እጅግ የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳት ያሉትን የእርዳታ አማራጮች እንዲያጤኑ” ትዕዛዝ መስጠታቸው ተናግረዋል፡፡

ሱሊቫን በመግለጫቸው “ዩናይትድ ስቴትስ ዛሬ በቱርክና ሶሪያ በደረሰው አውዳሚ ርዕደ መሬት እጅግ በጣም አሳስቦቷል፡፡ የሚያስፈልገውን እርዳታና ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጅ ሆነናል“ ብለዋል፡፡

በደረሰው አደጋ ስለሞቱትና ስለቆሰሉት ሰዎች መደንገጣቸውን የገለጹት የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለነስኪም መንግሥታቸው ድጋፏን እንደምትሰጥ ተናግረዋል፡፡

XS
SM
MD
LG