በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

 
አቡነ ፍራንሲስ እና ኢማም ሼክ አሕመድ ለጸጥታው ም/ቤት የሰላም መልዕክት አስተላለፉ

አቡነ ፍራንሲስ እና ኢማም ሼክ አሕመድ ለጸጥታው ም/ቤት የሰላም መልዕክት አስተላለፉ


የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንሲስ
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንሲስ

የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንሲስ እና በካይሮ የሱኒ አስተምህሮ ተቋም ታላቅ ኢማም የሆኑት ሼክ አሕመድ አል ጣይብ፣ ትላንት ረቡዕ ለተካሔደው የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ በላኩት መልዕክት፣ በዓለም ላይ፣ ለግጭት መቀስቀስ ምክንያት ነው ያሉትን “ጥላቻ” አውግዘው፣ የ“ወንድማማችነት” አስፈላጊነት ላይ ትኩረት በመስጠት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ጦርነት ይብቃ!”

ከተደረገላቸው ቀዶ ሕክምና በማገገም ላይ ያሉት አቡነ ፍራንሲስ በላኩት የጽሑፍ መልዕክት፣ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት፣ “ቀስ በቀስ” እየተካሔደ እንደኾነ ጠቁመው፣ የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች፥ ጥቅም ላይ የመዋል እና ጉዳት የማድረስ ዕድል አላቸው፤ ብለዋል። በመኾኑም፣ “ጦርነት ይብቃ!” ለማለት ጊዜው ደርሷል፤ ብለዋል።

አንድ ሺሕ ዓመት ያስቆጠረው በካይሮ የሚገኘው የሱኒ አስተምህሮ ማዕከል ታላቅ ኢማም ሼክ አሕመድ አል ጣይብ፣ በቪዲዮ ለጸጥታው ም/ቤት ጉባኤ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ለዓለም ሰላም የሰው ልጆች ወንድማማችነት ቁልፍ ነው፤ ብለዋል። ይህም፣ ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ አንድ ላይ በመሆን፣ እ.አ.አ በ2019 ካስተላለፉት መልዕክት ጋራ ተመሳሳይ እንደሆነ ተመልክቷል።

የም/ቤቱ የወሩ ፕሬዚዳንት የሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ሰላምን ለማምጣት የሰው ልጆች ወንድማማችነት ያለው ሚና፣ የወሩ ዋና መልዕክት እንዲሆን መርጣለች፡፡

ም/ቤቱ፣ የፖፑን እና የኢማሙን መልዕክት፣ እንዲሁም የአባላትን ንግግር ካደመጠ በኋላ፣ የጥላቻ ንግግር፣ ዘረኝነት፣ የመጤዎች ጥላቻ፣ ትዕግሥት ማጣት፣ የጾታ ልዩነት፣ ጽንፈኝነት፥ “ለግጭት መፈንዳት፣ መባባስ እና መደጋገም አስተዋፅኦ አድርጓል፤” የሚል የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

የአቋም መግለጫው በሙሉ ድምፅ ቢጸድቅም፣ አንዳንዶቹ የምክር ቤት አባል ሀገራት፣ በመግለጫው በአወገዟቸው ተግባራት እንደሚከሠሡ፣ አሶሽየትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG