የሮማ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንሲስ ሳንባቸው በመቆጣቱ በደም ሥር በሚሰጥ ፀረ ተሃዋስያን ህክምና እየተረዱ መሆናቸውን ቫቲካን አስታወቀች።
አቡኑ የቤተ ክህነት ቀጠሮዎችን ወደ ሌላ ጊዜ ማስተላለፋቸውንም ቤተክስያኒቱ አክላ ገልጣለች።
አባ ፍራንሲስ የሳምባ ምችም ይሁን የትኩሳት ህመም እንደማይስተዋሉባቸው ባለሥልጣናቱ አመልክተዋል።
እራሳቸውም ቢሆኑ የሳምባ መቆጣት እንዳደረባቸው ተናግረው ዘወትር ዕሁድ ረፋድ ላይ ለቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ምዕመንና ታዳሚ በመስኮት ሰላምታ የሚሰጡበትን ሥርዓት ትናንት ያልጠበቁበትን ምክንያት ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ቫቲካን ከሚገኘው መኖሪያቸው ፀሎተ-ቡራኬ አድርሰዋል።
የቫቲካን ፕሬስ ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር ማትዮ ብሩኒ ዛሬ በፅሁፍ ባወጡት መግለጫ ‘ህመሙ በአቡነ ፍራንሲስ የመተንፈሻ አካላት ላይ “መጠነኛ” ያሉትን ችግር መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ አቡኑ የጤና ሁኔታ አሳሳቢ አለመሆኑንና መዋዠቅ የማይታይበት መሆኑን፤ ትኩሳት እንደሌላቸውና ሁኔታቸው ግልፅ መሻሻል ማሳየቱን ብሩኖ አክለው ገልፀዋል።
አቡነ ፍራንሲስ የዛሬ 3 ሣምንት፤ ታኅሣስ 7 ሰማንያ ሰባት ዓመታቸውን ይደፍናሉ።
መድረክ / ፎረም