በኬንያ መንግሥት ላይ ትችት የሚሰነዝሩ ወጣቶች ላይ ያነጣጠረው አፈና እንዲቆም በሚጠይቁ የጎዳና ላይ ሰልፎች ላይ የተሳተፉ ተቃዋሚዎች እና አንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ሰኞ ዕለት መታሰራቸው ተገለጸ።
የኬንያ ምክር ቤት አባል የሆኑት ሴናተር ኦኪያ ኦምታታህ፣ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ ተቃውሞ ያካሄዱ እና ፖሊስ በዚህ ወር ያገታቸውን ሰባት ሰዎች እንዲለቅ የሚጠይቁ መፈክሮችን ያሰሙ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ተቀላቅለዋል።
ፖሊስ ተቃዋሚዎቹን ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ የተጠቀመ ቢሆን፣ ሴናተሩን ጨምሮ በርካታ ሰዎች እጅ ለእጅ ተቆላልፈው ከቦታው ለመነሳት ፈቃደኛ ባለመኾናቸው ለእስር መዳረጋቸው ተዘግቧል።
የኬንያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው ሐሙስ በአወጣው መግለጫ በመንግሥት ተቺዎች ላይ እየተፈፀመ ነው የተባለው አፈና እየጨመረ መሄድ እንዳሳሰበው ገልጾ ነበር። በሰኔ ወር ከተካሄደው የመንግሥት ተቃውሞ ሰልፍ ወዲህ 82 ተመሳሳይ ውንጀላዎች እንደደረሱትም አመልክቷል።
ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በበኩላቸው ወጣቶች በሰላም እንዲኖሩ መንግሥት አፈናውን እንደሚያስቆም ቅዳሜ ዕለት ገልጸው ነበር።
የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ከአፈናዎቹ ጀርባ ያለው የሀገሪቱ ፖሊስ መሆኑን በመግለፅ ክስ ቢያቀርቡም፣ ፖሊስ እጁ እንደሌለበት እና ደብዛቸው የጠፉ ሰዎች ጉዳይ ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።
መድረክ / ፎረም