በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል የተባለው የፖሊስ ባልደረባ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀበት


የኢድ አልፈጥር በዓል እየተከበረ በነበረበት ወቅት
የኢድ አልፈጥር በዓል እየተከበረ በነበረበት ወቅት

የኢድ አልፈጥር በዓል እየተከበረ በነበረበት ወቅት አስለቃሽ ጭስበማፈንዳት ተጠርጠሮ የተያዘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል አድማ ብተና ዘርፍ ባልደረባ ኮንስታብል አንቡላ ኡቴ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የ13 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለመርማሪ ፖሊስ ፈቅዷል። የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል አድማ ብተና ባልደረባ የሆነው ኮንስታብል አንቡላ ኡቴ ሚያዝያ 24 ቀን 2014 ዓ.ም በተከበረው የኢድ አልፈጥር በዓል ሥነ ስርዓት ላይ፤ በአዲስ አበባ ከተማ የቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሀውልት አካባቢ በተመደበበት ቦታ ላይ የአስለቃሽ ጭስ ቦንብ ማፈንዳቱን ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ምክኒያት አብራርቷል።

ለሁለተኛ ጊዜ ካለ ጠበቃ ፍርድ ቤት የቀረበው ተጠርጣሪዉ ግን ድርጊቱን ሆን ብሎ እንዳልፈፀመ አስረድቷል። “አስለቃሽ ጭሱ ሳላውቅ በድንገት ነው የፈነዳብኝ” ብሏል። ጭሱ ወደ ሕዝቡ እንዳይሄድ በማሰብ በድንጋጤ ወደ ሌላ አቅጣጫ መወርወሩንም ገልጿል።

በአካባቢው የነበሩ ሰዎች የፌዴራል ፖሊስ ደንብ ልብስ ለብሶ እያዩም ቢሆን አንገቱን አንቀው ድበደባ እንደፈጸሙበትና የግራ ዐይኑና ኩላሊቱ ላይ ጉዳት እንዳደረሱበትም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። ተጠርጣሪውን ይዘው የቀረቡ ሁለት መርማሪ ፖሊሶችም እስካሁን ያከናወኑትን የምርመራ ሥራ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

ባለፉት 10 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ውስጥ በተጠርጣሪው የግል ስልክ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም ለኢትዮ ቴሌኮም ደብዳቤ መፃፋቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም ተጠርጣሪው የፋይናንስ ድጋፍ እንዳለው እና እንደሌለው ለማጣራት ለባንኮች ደብዳቤ መጻፋቸውን አክለው ጠቅሰዋል።

የሦስት ግለሰቦችን የምስክርነት ቃል መቀበላቸውን እንዲሁም የሥራ ኃላፊዎችን ቃል መቀበላቸውንም አብራርተዋል። መርማሪዎቹ አክለውም ተጠርጣሪው በዕለቱ አንድ ብቻ ሳይሆን ሦስት የአስለቃሽ ቦንቦች ማፈንዳቱን ተናግረዋል።

ከፍንዳታው በፊት ከአንዲት ሴት ጋር በአካል ማውራቱን እንዲሁም ሰልክ ተደውሎለት ሲያወራ እንደነበርም ገልጸዋል። ከደቡብ ክልል ዳዋሮ ዞን ለሥራ እንደ መጣ የገለፀው ተጠርጥረው በበኩሉ ጠያቂ እንደሌለው፣ ወላጆቹ በሕይወት እንደሌሉና ታናሽ ወንድሙን እያስተዳደረ መሆኑን አስረድቶ የዋስትና መብት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ግብር አበሮቹን በማፈላለግ ላይ መሆኑን ገለፆ የዋስትና መብት እንዳይሰጠው በማለት ለተጨማሪ 14 ቀን ምርመራ እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። ግራ ቀኙ ያዳመጠ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የ13 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀዷል።

ፍርድ ቤቱ ለግንቦት 23 ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። በኢድ አልፈጥር በዓል አከባባር ላይ በተፈጠረው ችግር በመስቀል አደባባይ እና በአዲስ አበባ ስታድዮም አካባቢ በሚገኙ የመንግሥት እና የግል ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።

በዕለቱ በርካታ ሕፃናት በድንጋጤ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መጠፋፋታቸው እና በርካታ ግለሰቦችም በጭሱ መታፈናቸው ታይቷል።

XS
SM
MD
LG