ዋሺንግተን ዲሲ —
ትናንት ዋሺንግተን ውስጥ ዋይት ሃውስ አቅራቢያ በሚገኘው ላፋየት አደባባይ የሚገኘውን የፕሬዚዳንት አንድሩው ጃክሰን መታሰቢያ ሃውልት ለመጣል የሞከሩትን ተቃዋሚዎች ፖሊስ በኃይል አባሯቸዋል።
ተቃዋሚዎቹ ሃውልቱን በገመድ አስረው ሊጥሉት ሲሞክሩ የዩናይትድ ስቴትስ ፓርክ ፖሊስ አባላት ደርሰው በዱላና ለብላቢ ጋዝ በመርጨት አባረዋቸዋል።
ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ ይህንኑ ተከትሎ በትዊተራቸው ድርጊቱን አውግዘው በአርበኞች መታሰቢያ ጥበቃ ድንጋጌ 10 ዓመት እስራት ያስቀጣል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የሰባተኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መታሰቢያ ሃውልት ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው አስቀድሞ የነበራቸውን ወታደራዊ ሙያ የሚዘክር በሙሉ ወታደራዊ መለዮ ልብስ ፈረስ ላይ ሆነው የሚታዩበት ነው።
ሆኖም ፕሬዚዳንቱ በደቡባዊው የሀገሪቱ ክፍለ አያሌ ሺህ ነባር አሜሪካውያንን ከመሬታቸው በጉልበት እየተነቀሉ ለስደት እንዲዳረጉ ያረገውን የ1830ውን ህግ በመፈረማቸው ይነቀፋሉ።
ደግሞም ቴኔሲ ሁዳዳቸው ላይ በርካታ ባሮች እንደነበሩዋቸውና ብዙም ጊዜ አያያዛቸው ክፋት የተመላበት እንደነበር ተገልጿል።