በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አንጎላ የተካሄደው ተቃውሞ ሰልፍ


አንጎላ ዋና ከተማ ሉዋንዳ ውስጥ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተካሄዱትን ሁከት የቀላቀሉ ፀረ-መንግሥት የተቃውሞ ሰልፎች ተከትሎ ቢያንስ አንድ መቶ ሰዎች መያዛቸውን የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ገለጽ።

በዋና ከተማዋ የተጠራውና ወደ 2000 የሚጠጉ ሰዎች ያሳተፈውን የተቃውሞ ሰልፍ ለመበተን አድማ በታኝ ኃይሎች አስለቃሽ ጋዝ ረጭተዋል፣ ደብድበዋቸዋል።

ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ በዛፍ ግንድ፣ በትላልቅ ድንጋይ፣ በገመድና በእሳት በተያያዙ የመኪና ጎማዎች መንገዶችን ዘግተዋል። የሀገሪቱን ባንዲራ ያቃጠሉም እንደነበሩ ዘገባዎች ጠቅሰዋል።የአንጎላ የሃገር አስተዳደር ሚኒስቴር ከፍተና ባለሥልጣን በመንግሥቱ ቴሌቭዥን በሰጡት መገለጫ አንድ መቶ ሦስት ሰዎች የዋናው ተቃዋሚ ፓርቲ የዩኒታ አባላትም ጭምር ታስረዋል ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ብለዋል። ስድስት ፖሊሶች ላይ ጉዳት መድረሱንም ነው ባለሥልጣኑ የተናገሩት።

የተቃውሞ ሰልፉ የተጠራው እአአ በ2020 ዓመት መካሄድ ለነበረበት እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለዘገዩት የአካባቢ አስተዳደር ምርጫዎች አዲስ የጊዜ ሰሌዳ እንዲወጣ በመጠየቅ ሲሆን ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ የሥራ ዕድል እና የተሻለ የኑሮ ሁኔታም ይሰጠን ሲሉ ጠይቀዋል።

ዋናው የአንጎላ ተቃዋሚ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ ፖሊስ በተቃዋሚ ሰልፈኛው ላይ ከመጠን ያለፈ ኃይል ተጠቅሟል ብሎ አውግዟል። የታሰሩት ሰዎች ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ይልቀቁ ሲልም ጠይቋል።

XS
SM
MD
LG