በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለጠ/ሚኒስትር አብይ የተላኩ የደስታ መግለጫዎችና የቀጣይ ጊዜ ማሳሰቢያዎች


ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የ2012 ኖቤል የሰላም ሎሬት ኾነው መመረጣቸው ከተሰማ በኋላ ከመላው ዓለም የሚላኩ የደስታ መግለጫዎች ማኅበራዊ ሚዲያን በተለይም ደግሞ ትዊተርን አስጨንቀውት ውለዋል። የአገር መሪዎች፣ ታዋቂ የፖለቲካ ሰዎች፣ አምባሳደሮች በአጠቃላይ “ቀዳሚ” በሚባል ዘርፍ የሚሰለፉ አብዛኞቹ መልዕክታቸውን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰደዋል።

“ከእንኳን ደስ ያለዎ!” መልዕክት በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱን በቀጣይም ለበጎ ተግባር በማዋል በአገሪቱ የተከሰተውን አለመረጋጋት እንዲያስተካክሉና ሰላም እንዲያሰፍኑ ምክረ ሐሳብ የለገሱ ይገኙበታል።

ስለ ሽልማቱ በትዊተር ገፅ ላይ

“የዚች የተባረከች አገር ልጆች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ" የሚል መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ናቸው። "ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር ዓቢይ አሕመድ የ2019 የኖቤል ሠላም ሽልማትን አገኙ! እንኳን ደስ አሎት!እንኳን ደስ አለሽ እናት አገር ኢትዮጵያ! በአገራችን አራቱ ማዕዘን በዓለም ዙርያ የምትኖሩ የዚች የተባረከች አገር ልጆች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ" ብለዋል።

ከሽልማቱ በኋላ በትዊተር ገፃቸው በአጭሩ ምስጋናን ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ "ይህ ሽልማት የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ነው" ብለዋል። አያይዘውም "በኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ሰጪ ኮሚቴ ውሳኔ በጣም ተደስቻለሁ። ለሰላም ሲሉ ጠንክረው ለሚሠሩ ሁሉ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ" ብለዋል።

በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደታየው ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አሕመድ ኦስሎ ከሚገኘው የኖቤል ሽልማት ቢሮ ከኮሚቴው ጸሐፊ ስልክ ተደውሎ ማሽነፋቸው በተነገራቸው ወቅት፤ “በጣም ነው የማመሰግነው ዜናውን ስሰማ ከፍተኛ ክብር ተሰምቶኛል በደስታም ተንጫለሁ። በጣም አመሰግናለው! ይህ ለአፍሪካ ብሎም ለኢትዮጵያ የተሰጠ ነው፡፡ ሌሎች የአፍሪካ መሪዎችም በአህጉራችን ላይ ሰላም ለማስፈን በትጋት እንደሚሠሩ ይታየኛል፡፡ በጣም አመሰግናለው።” ሲሉ ምላሽ ምላሽ ሰጥተዋል።

በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር እስጢፋኖስ አፈወርቂ በትዊተር ገፅ ላይ ባሰፈሩት የመልካም ምኞችት መግለጫ መልዕክት፤ “ የኖቤልን የሰላም ሽልማት በማሸነፎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ እንኳን ደስ አሎት! የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በደም፣ በላብና በእንባ ላይ እንደገና ድልን ተቀዳጁ” ብለዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው “ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የ2019 ዓ.ም የኖቤል የሰላም ሽልማት ከኤርትራ ጋር ሰላምን በማምጣት ስለተጫወቱት ሚና በማሸነፍዎ እንኳን ደስ ያለዎ! ኢትዮጵያዊ በመሆኔ ኮራሁ።” ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ “ብዙ ጊዜ የተስፋ ንፋስ በአፍሪካ እየነፈሰ ነው እላለሁ። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክኒያቴ አብይ አሕመድ ነው” ብለዋል። አያይዘውም “የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ራዕይ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ታሪካዊ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አስችሏቸዋል። ባለፈው ዓመት ይህንን ስምምነት ሲፈራረሙ በቦታው በመኖሬ ደግሞ ክብር ይሰማኛል።” ሲሉ በመልካም ምኞት መግለጫው ላይ አስፍረዋል።

ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በመልዕክታቸው መጨረሻ፤ “ይህ አዲስ ምዕራፍም አካባቢው ደህንነትን እና መረጋጋትን የሚያሰፍን አዲስ ዕድሎችን ከፍቶለታል። እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በአመራርነታቸው ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና ከአፍሪካ ውጭ ላሉ መሪዎችም ግሩም ምስሌ መሆን ችለዋል።” ብለዋል።

የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል (NCR) ዋና ጸሐፊ ጃን ኢግላንድ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሽልማት መደሰታቸውን በመግለጫ ልከዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአገሪቱ ሰላምን ለማስጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት አጠንክረው እንዲቀጥሉም መልዕክት ልከዋል።

“ድርጅታችን የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል (NCR) በኢትዮጵያና በኤርትራ ከስደተኞች ጋር ከሚሰሩ ጥቂት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከል አንዱ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በሁለቱ ሃገራት መካከ ያመጡትን ለውጥ የዐይን እማኝ ሆነን ለማየት ችለናል። ይህ ለውጥ የመጣው ደግሞ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው ግጭትና ቁርሾ ዜጎች ለዓመታ በመፈናቀል ከተሰቃዩ በኋላ ነው” ብለዋል።

ዋና ጸሐፊ ጃን ኢግላንድ አያይዘውም አሁን የኖቤል የሰላም ሽልማት የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ የተከሰተውን የብሔር ፍጥጫ ቅድሚያ ሰጥተው በማስተካከል በሕዝቦች መካከል ሰላምን ለማምጣት መሥራት አለባቸው ብለዋል።

“የዛሬው ሽልማት የዶ/ር አብይ አሕመድ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ነው” ያሉት ጃን ኢግላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሽልማት ያሰጣቸውን በጎ ተግባር አጠናክረው ቀጥለው በሃገሪቱ የተከሰተውን የብሔር ውጥረትን በማርገብ የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ እንደሚያደርጉ ተስፋ እንዳላቸው ጠቁመዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኪሚቴ ሊቀመንበር የካሊፎርኒያ ዴሞክራቲክ እንደራሴ ኬረን ባስ የዶ/ር አብይን ማሸነፍ ለአፍሪካ ምሳሌ መሆኑን ጠቅሰው ለኢዮጵያውያን “ይገባችኋል” ብለዋል።

“የኖቤል የሰላም ሽልማት በማግኘታቸው የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን እንኳን ደስ ያለዎ ለማለት እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥና በመላ የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ቁርጠኝነታቸውን እያሳዩ ላሉት እጅግ ወጣቱ አፍሪካዊ መሪ ይህ ክብር በእውኑ ይገባቸዋል። ባለፈው ዓመት በአፍሪካ እጅግ ለተራዘመ ግዜ የዘለቀውን ግጭት ያስቆመውን በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተደረሰውን ስምምነት ለመፈረም ያሳዩት ደፋርነት በእውኑ አነቃቂ ነበር።” ይላል የኬረን ባስ መልዕክት።

አያይዞም ”ሰላምን ለመጨበጥ መተባበርን ለማጎልበት ዓለም አቀፍ የስደተኞች ሕግጋትን ለማክበር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የያዙት አቋም በመላ ዓለም ስደተኞቹን እያስተናገዱ ላሉ ሀገሮች ሁሉ አረአያ የሚሆን ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አመራር፤ ኢትዮጵያ የስደተኞችን የልደትና የጋብቻ የምስክር ወረቀቶችን በመመዝገብ የሥራ ፈቃድ እንዲያገኙና የመንጃ ፈቃድ ማውጣት እንዲችሉ በማድረግ ከኅብረተሰቡ ጋር ለመቀላቀል እገዛ እያደረገች ነው።” ሲሉ ምስጋናን ለግሰዋል።

“ሱዳን ውስጥ በሽግግሩ ወታደራዊ ምክር ቤትና በነፃነትና በለውጥ ኃይሎች መካከል ስምምነት ላይ እንዲደረስ በማሸማገል፣ በሶማሊያና በኬንያ መካከል ያለውን የባህር ላይ ይገባኛል ጥያቄ ለመፍታት በማደራደር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ያደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አካባቢውን ለመቀየርና የአፍሪካን የሁከት የግጭቶችና የድህነት ገፅታ ለመለወጥ ያላቸውን ከፍተኛ ጥራት ያሳያል። በርግጥ በአካባቢው አሁንም ብዙ ችግርች አሉ። ይሁን እንጂ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኖቤል የሰላም ሽልማት ሌሎችም የአፍሪካ መሪዎች በመላ አሕጉሪቱ ለሰላም ግንባታና ለእርቅ እንዲቆሙ ያነሳሳቸዋል የሚል እምነት አለኝ።” ብለዋል። በመጨረሻም “ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድና የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ- ይገባችኋል።” ብለው መልካም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ፤ "ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ እ.ኤ.አ በ2018 ዓ.ም ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ለሁለት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የነበረውን የድምበር ውዝግብ እልባት በመስጠት ሰላም ማውረድ የቻሉ መሪ መሆናቸውን አስታውሷል። ለዚህ ተግባራቸው የተሰጣቸው ሽልማት ተገቢ መሆኑን እንደሚያምን ድርጅቱ ገልፆ ከዚህ በኋላ ደግሞ ከፍተኛው ሥራ እንደሚጠብቃቸው ማስገንዘቢያ መልዕክት አስፍሯል።

“ይህ ሽልማት በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጋሬጣ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ይበልጥ ሊያበረታታቸው ይገባል” ያለው መግለጫው አያይዞም “በአፋጣኝ ሁኔታ በሃገሪቱ እየተፈጠረ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣አለመረጋጋትና የብሔር ግጭቶች እልባት መስጠት ይኖርባቸዋል” ሲል ማሳሰቢያ ይሰጣል።
"መንግሥታቸው በአገሪቱ ውስጥ ጫና ለመፍጠር እንደመሳሪያ እያገለገለ ያለውን የጸረ-ሽብር ህጉ በድጋሚ እንዲያፀድቅ እና ከዚህ በፊት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያደረሱ ተጠርጣሪ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ ማድረግ ይኖርበታል፡፡" ሲል አሳስቧል።
ዓለም አቀፍ የግጭቶች ጉዳይ አጥኚ ተቋም በበኩሉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ የ2019 ዓ.ም የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ በመሆናቸው ሞቅ ያለ የእንኳን ደስ ያለዎ መልዕክት አስተላልፈዋል፡”የጠቅላይ ሚኒስተሩ ድፍረት የተሞላበት አመራር በሃገር ውስጥና በውጪ በጎ ለውጥ ማምጣት ችሏል” ያለው የድርጅቱ መግለጫ፤ “ከኤርትራ ጋር ለመታረቅ ያደረጉት ጥረትም በሁለቱ አገራት መካከል ልዩ የሆነ መንገድ ጠርግዋል፡፡ ከአስመራ ጋር ቁርኝት መፈጠሩ እና የድንበር ግጭቱ መፈታቱ ጥርጣሬ ውስጥ የሚከታቸው አካላት እንደ መኖራቸው መጠን ብዙ ሥራዎችም መሠራት ይኖርባቸዋል፡፡ ይሁንና በጠቅላይ ሚኒስተሩ የተጀመሩት ነገሮች በአካባቢው መተባበር እና መረጋጋትን በመፍጠር አዳዲስ ዕድሎችን ፈጥረዋል፡፡” ይላል።

“በአገር ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተደረጉ ለውጦችም ወሳኝ ናቸው፡፡ በ2018 ወደ ቢሮ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ እርቅን ለማበረታታት የኢትዮጵያን የፌደራል ደህንነት አሠራር በመመርመር ያለፉ የመንግሥት በደሎችን አውግዘዋል፡፡ የፖለቲካ እስረኞችን ፈተዋል፡፡ ግልፅነት ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ለማስፈን ቃል በመግባት በስደት ላይ ያሉ ተቃዋሚዎችን ወደ አገራቸው አንዲመለሱ አድርገዋል፡፡ ቢሆንም ችግሮች አሁንም አሉ፡፡ በህብረተሰቡ መሃከል ውጥረቶች እያደጉ ነው፡፡ በአመራሮች መሃከል ያለውን ልዩነትን ማረጋጋትም አጣዳፊ መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን አንጂ የአብይ አህመድ አመራር ለሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የፈካ የወደፊት ተስፋ ነው፡፡

የተቋሙ ፕሬዘዳንት ሮበርት ማሌ “ ሃገራቸው ከኤርትራ ጋር የቆየችበት ባላንጣነትና በራሳቸው ሃገር የውስጥ አስተዳደር ላይ ገፁን ለመገልበጥ ባደረጉት ጥረት አዲስ ተስፋን ላመጡት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በሙሌ ልቤ እንኳን ደስ ያሎት እላለው፡፡ በእርግጥ ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት በማሻሻልም ሆነ ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት መደበኛ ለማድረግ እና በአገር ውስጥ ያለውን መሳሳብ በመዋጋት ረገድ ብዙ የሚሠሩ ነገሮች አሉ፡፡ አብይ ከኢትዮጵያውያንም ሆን ከዓለም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ቢሆንም ግን የኖቤል ሽልማቱ ለአገሪቱ ትልቅ ኩራት ነው” ብለዋል፡፡

የተቋሙ የአፍሪካ ዳይሬክተር ኮምፈርት ኢሮ በበኩላቸው ፤ “ይህ ሽልማት ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ላበረከቱተ ሥራ እውቀና የሚሰጥ ነው፡፡ ለአገሪቱም ሆነ ለአህጉሪቱ ብልፅግና ለማምጣት መነቃቃትን እና አዲስ ሃይልን የሚፈጥር መሆን አለበት” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አፍይ አሕመድ
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አፍይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ

የኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴው አሸናፊነታቸውን ይፋ ባደረገበት መግለጫ ፤ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ለሰላምና ለዓለም አቀፍ ትብብር ላደረጉት ከፍተኛ ጥረት የሽልማቱ አሸናፊ መሆናቸውን አብስሯል።

አምስት አባላት ያሉት የኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ሰጪ ኮሚቴ ሰብሳቢ በርቲ ረኢስ አንደርሰን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሽልማቱን አሸናፊ መሆናቸውን ሲያበስሩ፤ አብይ አሕመድ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለ20 ዓመታት የነበረውን የድንበር ይገባኛል ውዝግብና አለመግባባት ሥልጣን በያዙ በወራት ጊዜ ውስጥ በመፍታት ሰላም አምጥተዋል። በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ቁርሾም በመፍታት ለእርቅና ለሰላም በማብቃታቸው የዘንድሮው የ2012 ኖቤል የሰላም ሎሬት ሆነው ተመርጠዋል።

ይህ ኮሚቴ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ለሽልማት ያበቋቸውን በጎ ተግባራት በዘረዘረበት ምዕራፍም “ አብይ ገና ወደ ሥልጣን በመጡበት በመጀመሪያው 100 የሥልጣን ቀናት በሀገሪቱ ላይ ተጥሎ የነበረውን አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እንዲነሳ አድርገዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ከእስር ተፈተዋል፣ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ተጥሎ የነበረው ቅድመ ምርመራ እንዲቀር ተደርጓል። በውጭ አገር ነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲ ቡድኖች ወደ አገር ውስጥ ገብተው በሰላማዊ መንገድ የሚሠሩበትን ሁኔታ አመቻችተዋል፣ በሙስና ሲጠረጠሩ የነበሩ የወታደራዊ አመራሮችና ባለስልጣኖችን ከሥልጣን እንዲነሱ አድርገዋል እንዲሁም የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲጨምር አድርገዋል” ይላል።

በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደታየው ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አሕመድ ኦስሎ ከሚገኘው የኖቤል ሽልማት ቢሮ ከኮሚቴው ጸሐፊ ስልክ ተደውሎ ማሽነፋቸው በተነገራቸው ወቅት፤ “በጣም ነው የማመሰግነው ዜናውን ስሰማ ከፍተኛ ክብር እና መደናገጥ ተሰምቶኛል:: በጣም አመሰግናለው! ይህ ለአፍሪካ የተሰጠ ለኢትዮጵያ የተሰጠ ነው፡፡ ሌሎች የአፍሪካ መሪዎችም በአህጉራችን ላይ ሰላም ለማስፈን በትጋት እንደሚሠሩ ይታየኛል፡፡ በጣም አመሰግናለው፡ በጣም ተደስቻለሁ ደግሞም በዜናው ተደናግጫለሁ፡፡” ሲሉ ምላሽ ምላሽ ሰጥተዋል።

የኖቤል ሽልማት ኮሚቴው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአገሪቱ ጠንካራ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ለሚሠሩት ሥራም እውቅና ሰጠቷል። የበለጠ ደግሞ በኢትዮጵያና በኤርትራ የተካሄደው የሰላም ስምምነት ለሁለቱም አገሮች በጎ ለውጥን አስገኝቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከዚህ በተጨማሪ በምስራቅና በሰሜን አፍሪካ ሰላም ለማስፈን ያከናወኑት በጎ ተግባር በጉልህ የሚጠቀስ እንደሆነ ኮሚቴው አፅንኦት ሰጥቶታል። የኖቤል የሰላም ሽልማቱ ከዓለም አቀፍ እውቅናው በተጨማሪ 900 ሺሕ ዶላር የገንዘብ ሽልማትም አለው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ሽልማታቸውን በመጪው በመጪው ታኅሣሥ ወር ኦስሎ ተገኝተው ሽልማታቸውን ይወስዳሉ ተብሏል።

በተያያዘም የዓለም አቀፍ ታዋቂ የሰብዓዊ መብት ድርጅት መሪዎች፣ የአገር መሪዎች፣ አምባሳደሮችና ታዋቂ ሰዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የደስታ መግለጫ መልዕክት እያስተላለፉ ነው።

ለዚህ ከፍተኛ የኖቤል ሽልማት 301 እጩዎች ቀርበው ነበር። ዕጩዎቹ 223 ግለሰቦችና 78 ድርጅቶችም ነበሩ።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG