በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፒተር ሃይንላይን ተፈታ


በአወሊያ መስጊድ የተሰበሰቡ ሙስሊም አማንያን
በአወሊያ መስጊድ የተሰበሰቡ ሙስሊም አማንያን

በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የነበሩት የአሜሪካ ድምፅ የአዲስ አበባ ዘጋቢ ፒተር ሃይንላይን እና አስተርጓሚው ስመኝሽ የቆየ ዛሬ ተፈቱ፡፡

ፒተር አንድ ቀን እሥር ቤት አድሮ እንደወጣ በሰጠው መግለጫ ስመኝሽ በፆታዋ ምክንያት በፖሊስ ጣቢያው ውስጥ ልታድር የምትችልበት ሁኔታ ስላልነበረ እቤቷ አድራ ዛሬ ጠዋት ፖሊስ ጣቢያ እንድትቀርብ ተነግሯት ትናንት ማታ የተለቀቀች መሆኑን ተነግሯል፡፡

ፖሊስ ፒተርንና ስመኝሽን ያሠራቸው ትናንት በአወሊያ መስጊድ የተሰበሰቡ ሙስሊም አማንያንን ጉዳይ ለመዘገብ እዚያ ቆይተው ሲወጡ ነው፡፡

ፖሊስ ፒተር ሃይንላይንንና ስመኝሽን ያሠረው ሕገወጥ ዘገባ እያካሄዳችሁ ነው በሚል ነበር፡፡

ፒተር ሃይንላይን

ፒተር ስለተካሄደበት ምርመራ ሲናገር “አንድ የፖሊስ መኮንን ምርመራ አደረገብን እና ሕገወጥ ዘገባ እያካሄድን እንደነበረ ነገረን፡፡ እኛ የሄድንበት ወይም የተገኘንበት ቦታ ችግር ያለበት እና ሪፖርተሮች እዚያ የሚሄዱበት ምክንያት እንደሌለ ነገረን፡፡ የተራዘመ ምርመራ ነው የተደረገብን፡፡ ስለዘገባ አፃፃፍ፣ ወደዚያ መስጊድ ለምንና እንዴት ልንሄድ እንደቻልን፣ ዓላማችን ምን እንደነበረ ብዙ ምርመራ አደረገብን፤ ብዙ ማብራሪያም ሰጠን፡፡” ብሏል፡፡

አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ኮንሱላር ክፍል ባለሥልጣን ፖሊስ ጣቢያ ከመጡ በኋላ እርሱና ስመኝሽ መለቀቃቸውና ክሦቹ ሁሉ ውድቅ መደረጋቸው የተነገራቸው መሆኑን ሃይንላይን አመልክቷል፡፡

ስመኝሽ የቆየ

የተያዙ ጊዜ የተወሰዱባቸው ኮምፕዩተርና የመቅረጫ መሣሪያዎች ተመልሰውላቸዋል፡፡

ሃይንላይን በመለቀቁ እፎይታ የተሰማው መሆኑን የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጣቢያ ዋና መ/ቤት ዛሬ ማለዳ ላይ ከዋሽንግተን ዲ.ሲ. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

“ሃይንላይን - ይላል የቪኦኤ መግለጫ - በሙያ የተካነና እጅግ የተከበረ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ዓላማው ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚካሄዱ ጉዳዮች ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃን ማድረስ ነው፡፡ በሚስተር ሃይንላይን ላይ እንደተፈፀመው ዓይነት ጋዜጠኞችን የማዋከብ አያያዝ ያሳስበናል፡፡ ሥራቸውን ያለጣልቃገብነት ሥጋት ወይም ፍርሃት ማከናወን እንዲችሉ እንዲያደርግ ለመንግሥት ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡”

የዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ድርጅት - ሲፒጄ የምሥራቅ አፍሪካ ቃል አቀባይ ታም ሮድስ ዛሬ ለቪኦኤ በሰጠው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ዘጋቢዎችን ለመቻል ያለው ዝግጁነት እየጠበበ መምጣቱ ድርጅቱን እያሣዘነው እንደሆነ ተናግሯል፡፡

ሮድስ በማከልም “ፒተር ሃይንላይንን ዛሬ በመልቀቃቸውና የተራዘመና የተሣሣተ ወይም ጎርበጥባጣ ሂደት ውስጥ አለመገባቱ እዚህ ሲፒጄ ውስጥ ያለን ሰዎችን እጅግ በጣም አስደስቶናል፡፡ ይሁን እንጂ ቀድሞም ቢሆን መታሠሩ እራሱ በጣም አሣዝኖናል፡፡ አሁንም ቢሆን ይሄ የሚያሳየው ሊያስሩት የሚያስችላቸው እንዳችም እውነተኛ ምክንያት የሌላቸው መሆኑን ነው…” ብሏል፡፡

ሃይንላይን እንደሚለው የታሠረው በኢትዮጵያ የሙስሊም ማኅበረሰብ አመራር ጉዳይ ላይ ከመንግሥት ጋር ያለውን ውዝግብ እየዘገበ የነበረ በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡

እርሱና ስመኝሽ ሳያውቁ ጋዜጠኞች ወደውይይቱ እንዳይገቡ ፖሊስ ዘርግቶት የነበረውን የክልከላ መስመር ማለፋቸውን አመልክቷል፡፡

ከዚያ ሲወጣ ፖሊስ አስቁሞት ለጥያቄ በሚል ወደማዕከላዊ ፖሊስ ጣቢያ የወሰዱት መሆኑን ገልጿል፡፡

ፒተር ሃይንላይን ተቀማጭነቱ አዲስ አበባ የሆነ የቪኦኤ የምሥራቅ አፍሪካ ዘጋቢ ሲሆን ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጣቢያ ላለፉት ሃያ አራት ዓመታት ሠርቷል፡፡

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡



XS
SM
MD
LG