በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቀይ ባሕር ላይ በመርከቦች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የሚከላከል ዓለም አቀፍ ኅይል ተቋቋመ


የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስተን
የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስተን

ዩናይትድ ስቴትስ እና ሌሎችም ሀገሮች አንድ ላይ ሆነው ቀይ ባሕር ላይ በሚጓዙ መርከቦችን ከጥቃት ለመጠበቅ ዓለም አቀፍ ኅይል ሊያቋቁሙ መሆኑ ተነገረ፡፡ መርከቦቹ ላይ በሁቲዎች ቁጥጥር ሥር ካሉ የየመን አካባቢዎች በአብራሪ አልባ አውሮፕላኖች እና በተወንጫፊ ሚሳይሎች ጥቃት ሲሰነዘርባቸው ቆይቷል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስተን ዓለም አቀፉ ኅይል እንደሚቋቋም ዛሬ ማክሰኞ ባህሬን ውስጥ አስታውቀዋል፡፡ “ፕሮስፐሪቲ ጋርዲያን” ( Prosperity Guardian) ተብሎ በተሰየመው ዓለም አቀፍ ኃይል ብሪታኒያ፡ ባህሬን፡ ካናዳ፡ ፈረንሳይ ፡ ጣሊያን፡ ኔዘርላንድስ፡ ኖርዌይ፡ ሲሼልስ እና ስፔን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ሆነው የመርከቦቹን ደህንነት ይጠብቃሉ፡፡ አንዳንዶቹ በጋራ ቅኝት የሚያካሂዱ ሲሆን ደቡባዊ ቀይ ባሕር እና ኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ የጥበቃ ድጋፍ የሚሰጡም ኅይሎች እንደሚኖሩ ተመልክቷል፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የዩስ መከላከያ ሚንስቴር ባለስልጣን እንዳሉት በዓለም አቀፍ ኃይሉ ለመሳተፍ የተስማሙ ነገር ግን ስማቸው እንዲገለጥ ያልፈለጉ ሌሎችም ሀገሮች አሉ፡፡

ቀይ ባሕር ላይ በሚደርሱት ጥቃቶች የተነሳ በርካታ የጭነት መርከብ ኩባኒያዎች መርከቦቻቸው የጸጥታ ሁኔታው መፍትሄ እስከሚያገኝ ድረስ ባብ ኤል መንደብ ሰርጥ ሳይገቡ ባሉበት ቆመው እንዲጠብቁ አዝዘዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ኃይል ማዕከላዊ ዕዝ እንዳስታወቀው ትናንት ሰኞ ሁለት ተጨማሪ ጥቃቶች ደርሰዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስተን በመግለጫቸው “ይህ የጋራ እርምጃ የሚጠይቅ ዓለም አቀፍ ፈተና ” እንደሆነ አመልክተው “በመሆኑም ይህንን ታላቅ የደህንነት ተልዕኮ “ፕሮስፔሪቲ ጋርዲያን” መቋቋሙን ይፋ አደርጋለሁ” ብለዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በመርከቦቹ ላይ የሚደርሱትን ጥቃቶች በሚመለከት የተ መ ድ የጸጥታ ምክር ቤት እርምጃ እንዲወስድ ዩናይትድ ስቴትስ አሳስባለች፡፡ በመንግሥታቱ ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ለጸጥታ ምክር ቤቱ አባላት በላኩት ደብዳቤ ሁቲዎች በዓለም አቀፋዊው የባሕር መስመር ላይ ሕጉን ተከትለው በሚተላለፉ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ይህ ድርጊት የመርከብ ጉዞ መብት እና ነጻነትን እንዲሁም የዓለም አቀፍ የባሕር ጉዞ (ማሪታይም) ደሕንነት እና ዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ስጋት መደቀኑን ቀጥሏል” ማለታቸውን አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

የጸጥታ ምክር ቤቱ አባላት የየመን ሁቲዎች ስለደቀኑት ስጋት ትናንት ሰኞ በዝግ ስብሰባ የተወያዩበት ቢሆንም ወዲያውኑ እርምጃ አልወሰዱም፡፡

“ዩ ኤስ ኤስ ካርኒ” እና “ዩ ኤስ ኤስ ሜሰን” የተባሉ ሁለት የዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ኃይል አውዳሚ መርከቦች ከሁቲዎች የሚሰነዘረውን ጥቃት በመከላከል እና ምላሽ በመስጠት ለማገዝ በየቀኑ በባብ ኤል መንደብ ሰርጥ ያልፋሉ፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG