በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደቡብ አፍሪካ የታቀደው የሠላም ድርድር ተራዘመ


ፎቶ ፋይል፦ በአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት፤ አዲስ አበባ
ፎቶ ፋይል፦ በአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት፤ አዲስ አበባ

በኢትዮጵያ መንግሥትና በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ መካከል በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በደቡብ አፍሪካ ሊካሄድ የታቀደው የሠላም ንግግር ላልተወሰነ ግዜ መራዘሙን የዲፕሎማሲ ምንጮች አስታውቀዋል ሲል የቪኦኤው ፍረድ ሃርተር ከአዲስ አበባ ዘግቧል።

“ድርድሩ የተራዘመው ‘ከሎጂስቲክስ’ ወይም ከዝግጅት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች እና የውይይቱ ‘ፎርማት’ ወይም አካሄድ ላይ ገና ሥምምነት ላይ ባለመደረሱ ነው” ሲሉ የዲፕሎማሲ ምንጮቹ ለቪኦኤ ተናግረዋል።

ለውይይቱ ሌላ አዲስ ቀጠሮም አልተቆረጠለትም።

የኢትዮጵያ መንግሥት በውይይቱ ላይ እንደሚሳተፍ ማስታወቁ ይታወሳል። ህወሓትም በድርድሩ እንደሚሳተፍ አስታውቆ “ጥሪው ከመላኩ በፊት አላማከራችሁንም” በሚል አንዳንድ “ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው ጉድዮች” ያላቸውን አንስቷል።

ከነዚህም ውስጥ “እንደ ተሳታፊ፣ ታዛቢ፣ ዋስትና ሰጪ የሚሳተፉ ተጨማሪ ተዋንያን” ይኖሩ እንደሁ የጠየቀው ይገኝበታል። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ካለምንም ቅድመ ሁኔታና በማንኛውም ቦታ ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።

ድርድሩ በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሲጉን ኦባሳንጆ የሚመራ ሲሆን፣ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ፑምሴ ምላምቦ-ንኩካ የረዷቸዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት እና በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን ወይም ኢጋድ በታዛቢነት እንደሚገኙ የዲፕሎማሲ ምንጮች ለዜና ሰዎች ተናግረዋል።

ባለፈው ወር የትግራይ አማፂያኑ አመራር “ኤርትራ የኢትዮጵያን መንግሥት በመደገፍ በክልላችን ላይ ጥቃት አድርሳብናለች” ሲሉ ከሰዋል። ይህን ተከትሎም “እያንዳንዱ የትግራይ ተወላጅ” በውጊያው እንዲሳተፍ ጥሪ አድርገዋል።

በዚህ ሳምንት በትግራይ በአዲ ዳእሮ ላይ በተፈጸመ የአየር ድብደባ 65 ሲቪሎች መገደላቸውን የዕርዳታ ሠራተኞችና የትግራይ ኃይሎች ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ፣ የአየር ጥቃቱ የሚያነጣጥረው ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ነው ብሏል።

XS
SM
MD
LG