በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ታየ ደንድአ ታሰሩ


የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ደ’ኤታ አቶ ታየ ደንድአ
የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ደ’ኤታ አቶ ታየ ደንድአ

የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ደ’ኤታ አቶ ታየ ደንድአ ታሰሩ። አቶ ታየን ከኃላፊነታቸው ማንሳታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያሳወቁት ትናንት በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ባወጡት መልዕክት ነበር።

አቶ ታየ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የመንግሥቱን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረኃይል ጠቅሶ የመንግሥቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዛሬ ዘግቧል።

አቶ ታየ የተያዙት “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ይንቀሳቀሳሉ” ከተባሉና በመግለጫው ላይ በስም ካልተጠቀሱ “ኃይሎች ጋራ ተሳስረው ለጥፋት ተልዕኮ በኅቡዕ በመሥራት መንግሥታዊና የፓርቲ መዋቅሩን በመናድ ሴራ ተጠርጥረው ነው” ሲል ግብረኃይሉ ማሳወቁን ዘገባው ጠቅሷል።

አቶ ታየ “ሃገሪቱ ውስጥ ሲፈፀሙ ከነበሩ እገታዎች ጋራ እጃቸው እንዳለበት” መግለጫው ጠቁሞ “በማኅበራዊ ትስስር ገፆቻቸው ላይ “አፍራሽና ፀረ ሰላም ፅሁፎችን፣ ንግግሮችንና መግለጫዎችን በማውጣት” ከስሷቸዋል።

አቶ ታየ ትናንት ፌስቡክ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ “ጦርነት እንዲቆም ጥሪ በማቅረባቸውና ስለ እርቅ በመናገራቸው ከሥልጣናቸው መነሳቸውን” ገልፀው (እጠቅሳለሁ) “ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ” በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ብርቱ ወቀሳና ትችት አዘል ፅሁፍ፤ “የተናገሩትንና የፃፉትን የመደመር እሳቤ አምኜ ተከተልኩዎ፤ አሁን ግን በተናገሩት የማይኖሩ ብቻ ሳይሆኑ በሰው ደም የሚጫወቱ አረመኔ መሆንዎን ተረድቻለሁ” ብለዋል።

“እውነት መስሎኝ በሀገር ህልውና ስም ሲያካሂዱ የነበረውንና ኢትዮጵያዊያንን ከማገዳደል አልፎ አገሪቷን ያደቀቃትን ከንቱ ጦርነት ሳዳምቅልዎ በነበረበት ወቅት ሲያወድሱኝ ነበር፤” ያሉት አቶ ታየ “ዛሬ ነገሩ ገብቶኝ የወንድማማቾች መገዳደል ይቆም ዘንድ ለሰላም በመወገኔ ከሥልጣን አነሡኝ” ሲሉም ለስንብታቸው ምክንያት ነው ያሉትን አስፍረዋል።

“ለወንበር እና ለመኪና በመገዛት ኦሮሞን በኦሮሞ ለማጥፋትና ኦሮሞን ከወንድሞቹ ጋራ ለማጣላት የሚጫወቱትን ቁማር እያየሁ ዝም ባለማለቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ” ብለዋል የቀድሞው ሚኒስትር ደ’ኤታ አክለው።

አቶ ታየ ደንደአ ይህንን ሃሳባቸውን ካሰፈሩ በኋላ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የአሜሪካ ድምፅ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ሳይሳካ ቀርቷል።

የአቶ ታየ መታሰር ይፋ የተደረገበትና በአገር ውስጥ ሚድያ የተላለፈው የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረኃይል መግለጫ አቶ ታየ በተመደቡበት ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ሆነው “መንግሥትን ‘ገዳይ እና ጨፍጫፊ’ እያሉ በተደጋጋሚ እንደሚወቅሱ” ጠቅሷል። አክሎም “ሆኖም ከሽብርተኞች፣ ከፅንፈኞችና ከነፍስ ገዳዮች ጋር በተግባር የጥፋት ትስስር የነበራቸው ራሳቸው አቶ ታየ እንደሆኑ በተደረገ ክትትል ተረጋግጧል” ብሏል።

የግብረኃይሉ መግለጫ በመቀጠል “አቶ ታየ ከኦነግ ሸኔ አመራሮችና በሽብር ከተጠረጠሩ ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር ትስስር በመፍጠር መንግሥትን በዐመፅ፣ በሽብርና በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲያሴሩ ተደርሶባቸዋል” ሲል ወንጅሎ በኤግዚቢትነት የጠቀሳቸው “ኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች፣ የሰሌዳ ቁጥሮች፣ አርማዎች፣ ሰነዶችና ማስታወሻዎችን መኖሪያ ቤታቸው ላይ በተደረገ ፍተሻ ተገኝተዋል” ብሏል።

በሌላ በኩል ከአሥር ቀናት በፊት የሩብ ዓመት አፈፃፀሙን በተመለከተ የሰላም ሚኒስቴር ለተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት ከጋዜጠኞች ጋር ለአጭር ጊዜ ተነጋግረው የነበሩት የነበሩት አቶ ታየ ደንደአ “በየቦታው ያሉትን ግጭቶች ለመፍታት ሁሉም ወገን መሃል መንገድ ላይ ተገናኝቶ ሊሠራ እንደሚገባ” ምክር አዘል ሃሳብ ሰጥተው ነበር።

አቶ ታየ ከመታሰራቸው በፊት ያጋሩት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተፈረመው ደብዳቤ፤ “ከመስከረም 28/2014 ዓ.ም. ጀምሮ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ላበረከቱት አስተዋፅዖ እያመሰገንኹ ከታኅሣሥ 1/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነት የተነሡ መሆኑን አስታውቃለሁ” ይላል።

አቶ ታየ ሥራ ላይ ሆነውም በከፍተኛ ባለሥልጣንነት የነበሩበትን መንግሥት በተደጋጋሚ በመተቸት ይታወቃሉ። በቅርቡ “ጦርነት ይቁም፤ ሰላም ይስፈን” በሚል መሪ ቃል የተጠራ ሰላማዊ ሰልፍ መከልከሉን አስመልክቶ “የጦርነት ከበሮ በመታንበት አደባባይ ዜጎች በሰላማዊ ሰልፍ ጦርነትን እንዳይቃወሙ መከልከል መጥፎ ትርጉም ይሰጣል፤” ብለው ነበር።

አድማጮች በዚህ ጉዳይ ላይ በነገው ዕለት ሰፋ ካለ ትንታኔ ጋራ በሌላ ዘገባ እንመለሳለን።

ታየ ደንድአ ታሰሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:08 0:00

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG