በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ ከህወሓት ጋር ለመደራደር የሚያስችሉ ሁኔታዎችን እያጠናች መሆኑን ገለፀች


ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ከህወሓት ጋር የሚደራደረው ምን ዓይነት ሁኔታዎች ሲሟሉ እንደሆነ የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቁሞ በሥራ ላይ መቆየቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራው ኮሚቴ በ"10 እና በ 15 ቀናት ውስጥ" ለብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርት እንደሚያቀርብም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ለፓርላማ አባላት አስታውቀዋል።

"ኮሚቴው ሰላሙን በሚመለከት ኢትዮጵያ ምን ምን ትፈልጋለች? ምን ሲሳካ ነው የምንደራደረው? እንዴትስ ነው የምንነጋገረው? የሚለውን ጉዳይ ሲያጠና ቆይቷል።" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን አጥንቶ እስካሁን ሪፖርት አለማቅረቡን ተናግረዋል።

በብልጽግና ፓርቲ ሥራ አሰፈጻሚ ኮሚቴ መቋቋም በይፋ ሲነገር ይህ የመጀመሪያው ሲሆን፤ ተቋቁሟል የተባለው ኮሚቴ መቸ ሥራ እንደጀመረ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልጠቀሱም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮሚቴው የተሟላ ሪፖርት ይዞ ሲቀርብ ለሕዝብ በይፋ እንደሚታወጅም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የህወሓት አመራሮች እየተደራደሩ እንደሆነ ተገልጾ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ገፆች ላይ ሲዘዋወር የቆየውን ወሬ ተችተው፤ ውጊያውን ያልደበቀ መንግሥት ሰላም ለማምጣት ሲሆን የሚደብቀው መረጃ እንደሌለ ገልፀዋል።

“ጊዜ ሲደርስ እና ንግግር ሲጀመር እንናገራለን” ብለዋል።

ወደ ንግግር የሚገባ ከሆነ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚደራደረው ይሄው ኮሚቴ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ማብራሪያ አመልክተዋል።

/አድማጮች በዚህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ላይ የተሰናዳውን ሰፋ ያለ ዘገባ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ጠብቁን/

XS
SM
MD
LG