በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ምርጫ ቦርድ በተቃዋሚዎች ላይ የሚፈጸመው ወከባ እያወከኝ ነው ሲል መንግሥትን አማረረ


ምርጫ ቦርድ በተቃዋሚዎች ላይ የሚፈጸመው ወከባ እያወከኝ ነው ሲል መንግሥትን አማረረ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:54 0:00

ምርጫ ቦርድ በተቃዋሚዎች ላይ የሚፈጸመው ወከባ እያወከኝ ነው ሲል መንግሥትን አማረረ

በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ እየደረሰ ያለው ወከባ እና እንግልት፣ በሥራዬ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረብኝ ነው፤ ሲል ምርጫ ቦርድ አመለከተ።

ልዩ ልዩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በመንግሥት አካላት በሚደርስባቸው ጫና ምክንያት፣ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ማድረግ እንኳን እንዳልቻሉ የገለጹት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ፣ ችግሩ እንዲቀረፍ ቦርዱ ለመንግሥት ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ በማጣቱ ምክንያት፣ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ ይችሉ ዘንድ፣ በራሱ ስም አዳራሽ ለመከራየት መገደዱንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የ2015 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት የአፈጻጸም ሪፖርቱን፣ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡት፣ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለረዥም ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ እነዚኽን ችግሮች ለመቅረፍ የምክር ቤት አባላት ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ፣ ከምክር ቤቱ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ለተነሡላቸው ጥያቄዎችም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም፣ በፓርቲዎች ላይ የሚደርሱ ወከባዎችን ለመቅረፍ ቦርዱ ያለውን ቁርጠኝነት የተመለከተ ጥያቄ አንሥቷል፡፡

አቶ ውብሸት ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግሥት በሚደርስባቸው ጫና ምክንያት፣ አዳራሽ መከራየት እንኳን እንዳልቻሉ ገልጸው፣ ለቦርዱ ሥራም ጭምር ከፍተኛ እክል ነው ያሉትን ይህን ችግር ለመፍታት፣ በቦርዱ ስለተከናወኑ ተግባራት አብራርተዋል፡፡

ቦርዱ፣ ሚኒስትር ዴዔታ እና ከዚያ በላይ ሥልጣን ያለው የገዢው ፓርቲ ተወካይ፣ እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች ያሉበት የሦስትዮሽ ኮሚቴ ጭምር በማቋቋም፣ ለችግሮች እልባት ለመስጠት ያደረገው ጥረት፣ ተፈላጊውን ውጤት እንዳላመጣ የገለጹት ምክትል ሰብሳቢው፣ የተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከምርጫ ቦርድ ያለፉት ዘጠኝ ወራት ክንውኖች መካከል፣ ዐዲስ ክልል ለማደራጀት፣ በደቡብ ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች የተካሔደው ሕዝበ ውሳኔ ተጠቅሷል፡፡

ውጤቱ እንዲሻር ተወስኖ በቅርቡ በድጋሚ ይካሔዳል የተባለውን የወላይታ ዞን ሕዝበ ውሳኔ አስመልክቶም፣ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በቀጣይ የሚከናወነው ሕዝበ ውሳኔም፣ 250 ሚሊዮን ብር እንደሚወጣበት የገለጹት አቶ ውብሸት አየለ፣ መሰል ችግሮች ከተከሠቱበት በድጋሚ እንደሚሰረዝ አበክረው አሳስበዋል፡፡

የዚኽ ዘገባ ሙሉ ይዘት፣ በተያያዘው የቪዲዮ ዘገባ ላይ ይገኛል።

XS
SM
MD
LG