በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አብዛኛዎቹ የቶሌ ጥቃት ተጎጂዎች ከአንድ በላይ የቤተሰብ አባሎቻቸውን ማጣታቸውን ገለጹ


ከጎግል ካርታ ላይ ስክሪን ቅጂ የተወሰደ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ አካባቢን የሚያሳይ
ከጎግል ካርታ ላይ ስክሪን ቅጂ የተወሰደ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ አካባቢን የሚያሳይ

- ምክር ቤቱ አጣሪ ቡድኖችን አሠማራ

በኦሮምያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ በተባለ ቀበሌ ከተፈጸመው ትጥቃዊ ጥቃት የተረፉ ተፈናቃዮች፣ የቤተሰብ አባሎቻቸው በጅምላ ጥቃት እንደተገደሉባቸው ገለጹ።

ቤተሰቦቻቸውን በግድያው እንደተነጠቁ የተናገሩትን ተፈናቃዮች በስልክ ያነጋገርናቸው ሲኾን፣ አብዛኛዎቹ ከአንድ በላይ እንዳጡ ይናገራሉ። ባለቤቷ እና የኹለት ዓመት ልጇ በጥቃቱ እንደተገደሉባት የገለጸችልን አንዲት እናት፣ በእቅፏ የነበረችን የኹለት ዓመት ልጇንም በግድያው ማጣቷን አስታውቃለች። አምስት የቤተሰባቸውን አባላት እንዳጡ የገለጹ ሌላ ግለሰብም፣ "በአጥፊዎች ላይ ርምጃ ይውሰድ፤" ሲሉ አሳስበዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሠ ጫፎ፣ ከምክር ቤት አባላት የተውጣጡ ኹለት ቡድኖችን በማቋቋም፣ በጋምቤላ ክልል እና በኦሮምያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ውስጥ፣ በንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ግፎችን እንዲያጣሩ ስምሪት እንደሰጡ ታውቋል።

በሌላ በኩል፣ የምዕራብ ወለጋ ዞን ቡሳ ጎኖፋ፣ በጊምቢ ወረዳ ውስጥ ባለፈው ሳምንት በተፈጸመው ጥቃት የተጎዱ ሰዎችን በመርዳት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሶ፣ ድጋፉ ግን በቂ እንዳልኾነ አስታውቋል።

የዞኑ ጸጥታ እና አስተዳደር ጽ/ቤት በበኩሉ፣ "የጸጥታ ኃይሉ በአካባቢው ተሠማርቶ ጥበቃ እያደረገ ነው፤" ብሏል። ጥቃቱ እንዲፈጸም መረጃ በመስጠት ተባብረዋል በሚል የተጠረጠሩ በቁጥር ያልገለጻቸው ግለሰቦችም ተይዘው ምርመራ እየተካሔደባቸው እንደሚገኝ ጨምሮ አስታውቋል።

/ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ያዳምጡ/

XS
SM
MD
LG