በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፈረንሣይ ውስጥ ሁለት ሰው ተገደለ፤ ሰባት ተያዘ


ሳን ዱኒ በምትባል የሰሜናዊ ፈረንሣይ ከተማ ውስጥ በተካሄደ ፀረ-ሽብር ዘመቻ ቢያንስ ሁለት ሰው ተገድሎ ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

ሳን ዱኒ ከተማ ውስጥ ዛሬ ማለዳ ላይ ከሞቱት ሁለቱ አንደኛዋ ሕይወቷ የጠፋው ፖሊስ ባደረገው ከበባ ለሰባት ሰዓታት ከዘለቀው መፋጠጥ በኋላ የለበሰችውን በፈንጂ የታጨቀ ሰደርያ እራሷ ላይ በማፈንዳቷ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

ከበባው በተካሄደበት የከተማዪቱ ማዕከል ላይ ይገኝ ከነበረው አፓርታማ ሰባት ሰዎች ተይዘው ተወስደዋል፡፡

ፖሊስ እርምጃውን የወሰደው የቤልጅግ ዜጋ የሆነውና 129 ሰው የተገደለበት የዓርቡ የፓሪሱ ጥቃት ፈጣሪና መሪ ነው የተባለውን ጂሃዲስት አብደልሃሚድ አቡድን ለማደን እንደነበረ የፓሪስ አቃቤ ሕግ ፍራንሷ ሞላ ተናግረዋል፡፡

በቁጥጥር ሥር የሚገኙትንና ሕይወታቸው የጠፋውን ሰዎች ማንነት ለማጣራት የምርመራ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ሞላ ገልፀዋል፡፡

ምናልባትም ሰዎቹ እነማን እንደሆኑና እንደነበሩ ማምሻውን ሳይታወቅ አይቀርም ብለው ነበር፡፡

ስሙ ከሌሎችም የሽብር ጥቃቶች ጋር ተያይዞ የሚነሣው አቡድ በቅርቡ ሦሪያ ውስጥ እንደነበረ ተገልጿል፡፡

በዚህ የፈረንጅ ዓመት ውስጥ አቡድ ቢያንስ አንድ ጊዜ ወደ ሌላ የአውሮፓ ሃገር ተጉዞ እንደነበር የሚጠቁም መረጃ እንዳለ የታወቀ ሲሆን ይህም እየተመለሱ ያሉ ጂሃዲስቶች አደጋ ይጥላሉ ተብሎ እየተሰጋ ባለበት ጊዜ የደኅንነት ጥበቃ ክፍተት መኖሩን እንደሚያሳይ ተገልጿል፡፡

የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ዛሬ ለሃገራቸው ከንቲባዎች ባደረጉት ንግግር የዓርቡን ጥቃት አድርሻለሁ ያለውን እሥላማዊ መንግሥት ቡድንን ለመውጋት በመንግሥቱ ይወሰዳሉ ያሏቸውን ተከታታይና ተያያዥ እርምጃዎች ዘርዝረዋል፡፡

ፈረንሣይ ዛሬም ሦስተኛ ዙር የአየር ድብደባ ሦሪያ ውስጥ ባሉ የእሥላማዊ መንግሥት ቡድን ይዞታዎች ላይ ያካሄደች ሲሆን የአየር ጥቃት አቅሟን ለማጠናከርም በሻርል ደ ጎል ስም የተሰየመችውን ጄት ተሸካሚ መርከብ ወደ ሜዲቴራኒያን ባህር አስገብታለች፡፡

ኦሎንድ አይሲልን ለመውጋት አሜሪካና ሩሲያን ጨምሮ ጠንካራና ግዙፍ ጥምረት እንዲመሠረት ጥሪ አሰምተዋል፡፡

የፈረንሣይ መንግሥት እስከ ነገ - ሐሙስ /ኅዳር 9/2008 ዓ.ም/ ፀንቶ ይቆያል ተብሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ለሦስት ወራት እንዲራዘም ይፈልጋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በተጨማሪም የፈረንሣይ ሕገ-መንግሥት ሽብር ፈጠራንና ሌሎችም የቀውስ ሁኔታዎችን መጋፈጥ በሚቻል ሁኔታ እንዲቀየር እየጠየቁ ነው፡፡ ይህ ሃሣባቸው ግን ከሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች የበረታ ነቀፌታ እያጋጠመው እንደሆነ ይሰማል፡፡

በሌላ በኩል ግን ከዓርቡ ጥቃት ጋር ንክኪ አላቸው የተባሉ ሰዎችና ተጠርጣሪዎችን የማደኑ እንቅስቃሴ አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን የብራስልስ ተወላጅ የሆነው ዋና ተጠርጣሪ ሳላህ አብዱሰላም አሁንም ሽሽት ላይ ሣይሆን አይቀርም እየተባለ ነው፡፡ ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

ፈረንሣይ ውስጥ ሁለት ሰው ተገደለ፤ ሰባት ተያዘ
please wait

No media source currently available

0:00 0:15:26 0:00

XS
SM
MD
LG