በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"በፓሪስ የበጋ ኦሊምፒክስ ውድድር ሽብርተኞች ጥቃት ሊሰነዝሩ ይችላሉ" ተባለ


ሽብርተኞች በመጪው ሐምሌ ወር ፓሪስ ላይ የሚካሄደውን የበጋ ኦሊምፒክስ ውድድር ለማደናቀፍ ጥቃት ሊያደርሱ እንደሚችሉ የሚገልጽ አዲስ ማስጠንቀቂያ ወጥቷል። ባለፈው ሳምንት የፈረንሳይ ባለስልጣናት ፓሪስ ውስጥ ያከሸፉትን የመሰለ ሴራም ጭምር ሊኖር እንደሚችል ተመልክቷል።

"ሪኮርድድ ፊዩቸር" የተባለው የሳይበር ደህንነት ቡድን ዛሬ ማክሰኞ ባወጣው ሪፖርቱ በፓሪስ የኦሊምፒክስ ውድድር ወቅት ሊኖር የሚችለው የሳይበር ጥቃት ስጋት እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም ከዚያ ይበልጥ የሚያሰጋው በአካል የሚሰነዘር ጥቃት መሆኑን አመልክቷል።

"በይበልጥ የሚያሰጋው ሽብርተኝነት፥ ኃይል ተጠቃሚ ጽንፈኝነት፥ ህዝባዊ አመጽ እና ረብሻ የቀላቀለ ተቃውሞን ጨምሮ ሊከሰት የሚችለው የአካላዊ ደህንነት አደጋ መሆኑን ገምግመናል" ሲል ሪፖርቱ አሳስቧል።

"ሽብርተኞች እና ኃይል ተጠቃሚ ጽንፈኞች በተለይም የእስላማዊ መንግሥት ቡድን እና የአል ቃይዳ ደጋፊዎች የፓሪስ ኦሊምፒክስን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች ለማድረስ ማሴራቸውን እና መቀስቀሳቸውን እንደቀጠሉ ጥርጥር የለውም" ሲል የሳይበር ደህንንነት ተቋሙ ሪፖርት አስገንዝቧል።

ሪፖርቱ አክሎም ለውድድሩ ወቅት በስፋት የደህንንት ጥበቃ ስርዐት ስለተዘጋጀ ሽብርተኞች ብዛት ያለው ህዝብ የሚጎዳ ጥቃት በስኬት ለማድረስ ምንም ዕድል የሚኖራቸው አይመስልም ብሏል ።

ቀደም ሲል የፈረንሳይ የደሕንነት ባለስልጣናት ቢያንስ ሁለት በፓሪስ ኦሊምፒክስ ላይ የሽብርተኛ ጥቃት ለማድረስ የተወጠኑ ሴራዎችን ማክሸፋቸውን እንዳስታወቁ ይታወሳል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG