የእስራኤል ኃይሎች በእስራኤል ቁጥጥር ስር በሚገኘው ዌስት ባንክ ሸማቂዎችን ለመያዝ ባደረጉት አሰሳ ወቅት ዘጠኝ ፍልስጤማውያንን ገድለው ሌሎች በርካቶችን ማቁሰላቸውን የፍልስጤም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የዛሬው ብጥብጥ ለወራት ከቀጠለው ግጭት ከሁሉ የከፋው ነው ተብሏል።
እንደ ፍልስጤም የጤና ጥበቃ ሚንስትር ተጨማሪ ገለጣ ግጭቱ የተካሄደው የሸማቂ ኃይሎች ጠንካራ ይዞታ በሆነው እና ላለፈው አንድ ዓመት የእስራኤል ጦር ወታደራዊ እንቅስቃሴ በቀጠለባት ዌስት ባንኳ ጄኒን የስደተኞች ካምፕ ባካሄዱት ብርቱ አሰሳ ወቅት ነው።
እስራኤል ‘የሸማቂዎችን መረብ ለመበጣጠስ የታለመ ነው’ በሚል በየምሽቱ በዌስት ባንክ ወታደራዊ አሰሳ ስታደርግ ቆይታለች።
ፍልስጤማውያን በበኩላቸው እርምጃውን የወደፊት ግዛታቸው ለማድረግ በሚያቅዷት እና እስራኤል ላለፉት ሃምሳ አምስት ዓመታት በኃይል በያዘችው ምድር የሚደረግ መስፋፋት አድርገው ያዩታል።