በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

‘ለፍልስጤም የሉአላዊ አገርነት እውቅና መስጠት ብቸኛው የሰላም መንገድ ነው’ - የስፓኝ ጠቅላይ ሚንስትር


የስፓኙ ጠቅላይ ሚንስትር ፔድሮ ሳንቼዝ
የስፓኙ ጠቅላይ ሚንስትር ፔድሮ ሳንቼዝ

ስፓኝ፣ ኖርዌይ እና አየርላንድ በዛሬው ዕለት የፍልስጤም ግዛትን እንደ አገር ሉአላዊ እውቅና በመስጠት እስራኤል አጥብቃ የተቃወመችውን ተመሳሳይ እርምጃ የወሰዱ ሌሎች ከ140 በላይ የሚሆኑ አገራት ተቀላቅለዋል።

የፍልስጤም አስተዳደርን ‘ወሰደ’ ላሏቸው ማሻሻያዎች ያሞገሱት እና በአንጻሩ “ገንቢ ለሆኑ እርምጃዎች አንዳችም ፍላጎት አላሳየም” ያሉትን የእስራኤልን መንግስት የወቀሱት የኖርዌዩ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኤስፐን ባርት አይድ ‘የሁለት አገራት መፍትሄ’ በመባል የሚታወቅውን ዕቅድ ለማሳካት እንዲሰራ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጥሪ አሰምተዋል። እቅዱ እስራኤል እና ፍልስጤም እንደ ሃገር ጎን ለጎን በሰላም መኖር የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር የጠይቅ ነው።

የስፓኙ ጠቅላይ ሚንስትር ፔድሮ ሳንቼዝ በበኩላቸው በዛሬው ዕለት በሰጡት አስተያየት ለፍልስጤም እንደ አገር እውቅና የመስጠቱ እርምጃ “በእስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን መካከል ሰላም ለማስፈን የታለመ ነው” ብለዋል።

"እስራኤል እና ፍልስጤም እንደ ሃገር የሕዝቦቻቸው ደህንነትው ተጠብቆ በሰላም የሚኖሩበት ሁኔታ ይፈጠር ዘንድ ብቸኛ መፍትሄ ነው ብለን ሁላችንም የምንቀበለው መንገድ ነው" ሲሉ ሳንቼዝ አክለዋል። አያይዘውም ለፍልስጤም እንደ ሃገር እውቅና ለመስጠት የወሰዱትን ውሳኔ “የሁለት አገራቱን መፍትሄ” የሚቃወመውን አሸባሪ ድርጅት ሃማስን ሙሉ በሙሉ ውድቅ የምናደርግ መሆናችንን የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

ስፓኝ፣ ኖርዌይ እና አየርላንድ ለፍልስጤም አስተዳደር ሉአላዊ አገርነት እውቅና ለመስጠት ያላቸውን ፍላጎት ባለፈው ሳምንት ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ያደረጉት። ይህንንም ተከትሎ አገሮቹ የወሰዱትን እርምጃ ለሃማስ የቀረበ ስጦታ ያለችው እስራኤል አምባሰደሮቿን ከሶስቱም ሃገራት በመጥራት ተቃውሞዋን ገልጻለች። በተያያዘ ዜና የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እስራኤል ካትስ ዛሬ ሲናገሩ "በአይሁዳውያን አላይ የዘር ማጥፋት እና የጦር ወንጀሎችን በማነሳሳት ከመተባበር የሚቆጠር ነው" ሲሉ የስፓኝ መንግስትን ወንጅለዋል።

በሌላ በኩል ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ምዕራባውያን ኃያላን መንግሥታት እና ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች አሁንም ለፍልስጤም አስተዳደር ሉአላዊ አገርነት እውቅና አይሰጡም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሃማስ የሚቆጣጠረው የጋዛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደዘገበው፣ ወራት ባስቆጠረው የእስራኤል እና የሃማስ ጦርነት እስካሁን ከ36, 000 በላይ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG