በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የፓኪስታኑ የቀድሞ ጠ/ሚ የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው


ፎቶ ፋይል፦ የቀድሞ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካን
ፎቶ ፋይል፦ የቀድሞ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካን

የቀድሞ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካን በመዲናይቱ ኢስላማባድ ጸረ-መንግሥት ሠልፍ በመምራት ላይ ሳሉ በተደረገባቸው የግድያ ሙከራ እንደቆሰሉ ተነግሯል።

የ70 ዓመቱ የተቃዋሚው ፒ.ቲ.አይ ፓርቲ መሪ የሆኑት ካን ቀኝ እግራቸው ላይ በጥይት እንደተመቱ ከፍተኛ ረዳታቸው የሆኑት ራዉፍ ሃሳን ለቪኦኤ ተናግረዋል።

በመሳሪያ በደረሰው ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል፣ በርካቶች እንደቆሰሉ ሃሳን ጨምረው ገልጸዋል።

ካን የፑንጃብ መዲና ወደሆነችውና ጥቃቱ ከደረሰበት 150 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደምትገኘው ላሆር የሚገኝ ሆስፒታል ተወስደዋል። ሃኪሞች ካን በጥሩ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል።

ካን መኪና ላይ ሆነው ሰልፉን እየመሩ ሳለ ጥቃት አድራሹ ከመሬት ወደ እርሳቸው ሲተኩስ ከሠልፉ የወጡ ናቸው የተባሉ ምስሎች አሳይተዋል።

የዓይን እማኞች እንዳሉት ጥቃት ፈጻሚው በአውቶማቲክ መሣሪያው በመተኮስ ላይ ሳለ፣ አንድ የሰልፉ ተሳታፊ ዘሎ ከያዘው በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል። በዚህ መሃል አንድ ሰልፈኛ በተተኮሰ ጥይት ተገድሏል። ከድርጊቱ በኋላ የተለቀቀ ነው በተባለ ቪዲዮ “ህዝብን በማሳሳት ላይ ናቸው” ያላቸውን ኢምራን ካንን መግደል ዓላማው እንደነበር ተጠርጣሪው ተናግሯል።

የካን የቅርብ ሰውና የላይኛው ም/ቤት አባል የሆኑት ፋይሳል ጃቬድም ከተጎዱት አንዱ ናቸው ተብሏል።

የክሪኬት ስፖርት ኮከብ የነበሩትና በኋላም የተቃዋሚ ፖለቲካኛ የሆኑት ካን የመተማመኛ ድምጽ በማጣታቸው ባለፈው ሚያዚያ ከሥልጣናቸው ቢሰናበቱም፣ ድርጊቱ ሕገ-ወጥ ነው በሚል ሲቃወሙ ሰንብተዋል።

XS
SM
MD
LG