ፓኪስታን ውስጥ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል በምዕመናን በተሞላ አንድ መስጊድ ውስጥ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ ፀሎት ላይ የነበሩ ቢያንስ 47 ሰዎች ተገደሉ።
የኺበር ፓኽቱንዃ ክፍለ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ማዕከላዊቱ ፔሻዋር በአጥፍቶ ጠፊ መፈፀሙ በተነገረው በዚህ ጥቃት ከተገደሉት ሌላ 140 የሚሆኑ መቁሰላቸው ተነግሯል።
የአገሪቱ የፀጥታና ደህንነት ምክትል ኮሚሽነር ሻፊኡላ ኻን ከፍርስራሽ ውስጥ ሁለት ሰው በህይወት ማውጣታቸውን ማምሻውን ተናግረዋል።
በጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል አብዛኞቹ የክፍለ ግዛቲቱ ፖሊሶች መሆናቸው ተመልክቷል።
አደጋው የደረሰበት መስጊድ በደህንነትና የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚዘወትር መሆኑም ተነግሯል።