ፓክሲታን ውስጥ ዛሬ ረቡዕ በታገተው ጃፈር ፈጣን ባቡር ላይ በተካሄደ ወታደራዊ ዘመቻ የሠራዊቱ አባላት 190 ተሳፋሪዎችን ሲታደጉ 30 አሸባሪዎችን መግደላቸው ተገለጸ።
ርምጃው የተወሰደው ደቡባዊ የባሎቺስታን ግዛት ውስጥ ትላንት በተካሄደበት ጥቃት ለ24 ሰዓታት ዋሻ ውስጥ እንዲያድር የተገደደውን ባቡርና ተሳፋሪዎችን ለማስለቀቅ በተደረገ ጥረት ነው፡፡
ወደ 450 የሚጠጉ ሰዎችን አሳፍሮ ከኩዌታ ወደ ፔሻዋር በመጓዝ ላይ የነበረው ባቡር የቦምብ እና የተኩስ ጥቃት የደረሰበት ትላንት ማክሰኞ መኾኑን ተነግሯል፡፡
ጥቃቱንም ተከትሎ ባቡሩ በሲቢ አቅራቢያ በሚገኝ ዋሻ ውስጥ ከ24 ሰዓታት በላይ ታግቶ እንዲቆይ መደረጉ ተገልጿል።
ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደው የባሎክ ነፃ አውጪ ጦር (BLA) 200 ታጋቾችን በተለይም የደኅንነት እና የስለላ አባላትን መያዙን ገልጾ፣ የፖለቲካ እስረኞች በ48 ሰዓት ውስጥ እንዲፈቱ ጠይቋል።
በጥቃቱ የተጎዱ በትንሹ 37 ሰዎች ህክምና እየተደረገላቸው ሲኾን ቆስሎ የነበረው የባቡሩ ሹፌር ሕይወቱ ማለፉ ተመልክቷል።
ባለሥልጣናት የአደጋ ጊዜ ቡድኖችን፣ የነፍስ አድን ባቡርን እና አምቡላንሶችን ወደ ቦታው ልከዋል፣ ነገር ግን አካባቢው ተራራማ በመሆኑ የስልክ መስመሮች ችግር ተደራሽነቱን ከባድ አድርጎታል።
የባሎክ ነፃ አውጪ ጦር በፓኪስታን ጥቃቱን አጠናክሮ በመቀጠሉ “ከሽብርተኝነት ጋራ በተያያዘ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት በ45 ከመቶ ከፍ ብሏል” ሲል ዓለም አቀፍ የሽብርተኝነት ጠቋሚ ድርጅት አመልክቷል።
ባሎክ ባሎቺስታን ውስጥ የተሰማሩ የፓኪስታን ባለ ሀብቶች እና የቻይና ኢንቨስትመንቶች የአካባቢውን ሕዝብ ይጎዳሉ በሚል ይቃወማል፡፡
ባሎክ በፓኪስታንና በዩናይትድ ስቴትስ በጸረ ሽብርተኝነት የተፈረጀ ድርጅት ነው፡፡
መድረክ / ፎረም