በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“ነብዩ መሐመድን ተሳድቧል” የተባለ ናይጄሪያዊ በድንጋይ ተወግሮ መገደሉ ቁጣ አሥነሳ


በሶኮቶ ግዛት ጉዋንዱ ወረዳ፣ ናይጄሪያ
በሶኮቶ ግዛት ጉዋንዱ ወረዳ፣ ናይጄሪያ

በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ፣ “ነብዩ መሐመድን ተሳድቧል” የተባለ ግለሰብ፣ በድንጋይ ተወግሮ እንደተገደለ፣ ባለሥልጣናት እና የመብት ተሟጋች ቡድኖች አስታወቁ። ድርጊቱ፥ በአካባቢው የሃይማኖት ነፃነትን አደጋ ላይ የሚጥል ነው፤ ያሉት የመብት ተሟጋቾቹ፣ ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኡስማን ቡዳ የተባለው ሟቹ ሉካንዳ ነጋዴ፣ ከትላንት በስቲያ እሑድ፣ በሶኮቶ ግዛት ጉዋንዱ ወረዳ የተገደለው፣ በገበያ ሥፍራ ከሌላ ነጋዴ ጋራ ሲከራከሩ፣ “ነብዩ መሐመድን ተሳድቧል፤” በሚል እንደሆነ፣ የፖሊስ ቃል አቀባይ አሕመድ ሩፋ፣ በአወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ከግድያው ስፍራ የተወሰዱና ነዋሪዎች ያጋሯቸው የቪዲዮ ምስሎች፣ ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ተሰብስበው፣ መሬት ላይ የወደቀውን ኡስማን ቡዳን ሲራገሙ እና ድንጋይ ሲወረውሩበት ያሳያሉ።

የፖሊስ ቃል አቀባዩ ስለጉዳዩ ሲያብራሩ፣ በሥፍራው የፖሊስ ኃይል ሲደርስ፣ “ሕዝቡ ተበትኖ፣ ጉዳት የደረሰበት ግለሰብ ራሱን ስቶ” እንዳገኘው ገልጸው፣ ወደ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ ሕይወቱ እንዳለፈ አብራርተዋል።

በአብዛኛው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በሚበዙበት ሰሜናዊ ናይጄሪያ የተፈጸመው ይኸው የደቦ ግድያ፣ የእምነት ነፃነትን አደጋ ላይ ይጥላል፤ በማለት፣ የመብት ተሟጋቾች ድምፃቸው እያሰሙ ነው። ናይጄሪያ የሚገኘው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ “መንግሥት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት አልሰጠም፤” ብሎ በመክሠሥ ባወጣው መግለጫ፣ እንደዚኽ ዐይነት ግድያዎች፣ ፍትሕ ሳያገኙ ከቀሩ፣ ሕግ ፊት ሳይቀርቡ በመንጋ የሚፈጸሙ ግድያዎችን ያበረታታል፤ ብሏል።

XS
SM
MD
LG