በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኦሳማ ቢን ላድን ማነው?


ከዓለም እጅግ ተፈላጊው አሸባሪ ኦሳማ ቢን ላድን ተገድሏል። የሃምሳ አራት ዓመቱ ሽብርተኛ መሪ ትናንት ዕሁድ ፓኪስታን ግዛት ውስጥ በሚገኝ ግቢ በዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎች መገደሉን ይፋ ያደረጉት ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ናቸው።




ከዓለም እጅግ ተፈላጊው አሸባሪ ኦሳማ ቢን ላድን ተገድሏል። የሃምሳ አራት ዓመቱ ሽብርተኛ መሪ ትናንት ዕሁድ ፓኪስታን ግዛት ውስጥ በሚገኝ ግቢ በዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎች መገደሉን ይፋ ያደረጉት ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ናቸው።

በዓለም ዙሪያ ቢያንስ በሦስት አህጉራት በተፈጸሙ አረመኒያዊ የሽብርተኛ ጥቃቶች የሚወነጀለው ኦሳማ ቢን ላድን በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ ከማናቸውም ትልቁ የአደን ዒላማ ሆኖ ቆይቷል።
እኤአ መስከረም አስራ አንድ ሁለት ሽህ አንድ ዓመተ ምህረት በኒውዮርክ እና በዋሽንግተን ከደረሱት ከባድ ጥቃቶች በኋላ ፕሬዚደንት ቡሽ የጥቃቶቹ ዋናው አቀናባሪ መሆኑ የታመነውን ኦሳማ ቢን ላድንን ፈልገን ማግኘታችን የማይቀር ነው ብለው በይፋ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።
ፕሬዚደንት ቡሽ እንዲህ ብለው ነበር።
”ይህ ሰው ለራሱ ስልጣን እና ለራሱ ጥቅም ሲል ስልጣኔ የሚመስል ነገርን ሁሉ ማጥፋት ይፈልጋል። እጅግ በጣም ክፉ ከመሆኑ የተነሳም ፥ እሱ ለራሱ ዋሻ ውስጥ ተደብቆ ወጣቶችን ራሳቸውን እንዲገድሉ ይልካል። ለማመን የሚያቅት ግድያ የፈጸመ ወንጀለኛ ከመሆኑም ሌላ ህሊናም ሆነ ነፍስ የሚባል የሌለው ነው።”
የሆነ ሆኖ ይህ የዓለም እጅግ ከፍተኛ የአደን ዒላማ አሸባሪነቱ ገጽታው ከሰላማዊና ምቾት ከተመላበት አስተዳደጉ ጋር በሰላ ሁናቴ የሚጋጭ ነው።
ከሳውዲያዊ የኮንስትራክሺን ኩባኒያዎች ከበርቴ አባት ከተወለዱ ከሃምሳ የሚበልጡ ልጆች አንዱ የሆነው ኦሳማ እኤአ በሺህ ዘጠኝ መቶ ሃምሳ ሰባት ዓመተ ምህረት መጋቢት መጋቢት ቀን ነው ተወለደ ፥ አባቱ እሱ ዕድሜው ገና በአስራዎቹ ውስጥ እያለ ነው የሞቱት።
ከዚያም በሳውዲ አረቢያ ከፍተኛ መደብ ውስጥ ከገዢው ንጉሣዊ ቤተሰብ ኣባላት ጋር ተቀራርቦ ተንቀባሮ አደገ ፥ እናም በምህንድስና ከፍተኛ ትምህርት ዲግሪውን ለማግኘት ትምህርቱን ቀጠለ፥ በዚህም በቤተሰቡ ኩባኒያ ውስጥ ወደመስራቱ አቅጣጭ እያመራ ይመስል ነበር።
በዚህ ሁኔታ ሲኖር በሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ ዘጠኝ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት አፍጋኒስታንን በወረረችበት ጊዜ፥ ቢን ላድን ህይወቱ እስከ ዘላለሙ ተቀየረ።
እንደበርካታ ሙስሊሞች፥ ቢን ላድን ሶቪየቶቹን ሊወጋ አገር ጥሎ ሄደ፥ የመጀመሪያ ተሳትፎው ዕርግጥ ለአፍጋኖቹ ሙጃሂዲን እስላማዊ ተዋጊዎች ማለትም ዩናይትድ ስቴትስም ትደግፋለች ለነበሩት ማለት ነው፥ ለአዲስ ምልምል ተዋጊዎች የስንቅና ትጥቅ ወይም የሎጂስቲክስ ዕገዛ በማድረግ ብቻ የተወሰነ ነበር።
በሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማኒያዎቹ ኣጋማሽ ላይ ግን ቢን ላድን ከቤተሰቡ ሃብት ድርሻውን የራሱን ሚሊሽያ ኃይል ሊያቋቁምበት ወሰነ፥ በኋላ አል ቃይዳ ከአረብኛ ሲተረጎም ቤዙ ወይም መሰረቱ ተብሎ ይታወቅ የጀመረውን መረቡን ማለት ነው።
ሶቪየቶች ከአፍጋኒስታን ከወጡ በኋላ ቢን ላድን ወደሀገሩ ይመለስ እንጂ ከአፍጋኒስታኑ ጦርነት የቀድሞ ተዋጊ ጉዋዶቹ ጋር ግንኙነቱን ጠብቆና በሌሎች እስላማዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ቀጥሎ ነበር የቆየው። ሌላው በህይወቱ አዲስ ምዕራፍ የሆነው በሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ኢራቅ የነዳጅ ሃብታም ጎረቤትዋን ኩዌትን ስትወርር ሳውዲ አረብያ የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች በግዛትዋ እንዲሰፍሩ መጋበዙዋ ነበር።
ቢን ላድን ቅዱሱ ምድር ብሎ ወደሚመለከታት ሀገር ሙስሊም ያልሆኑ መግባታቸውን የተመለከተው እስልምናን መዳፈር አድርጎ ነበር። ርምጃውንም አጥብቆ ሲቃወም ቆይቶ እና በዓመቱ በሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና አንድ ከሳውዲ አረብያ ተባረረ። እነሆም ቢን ላድን ሱዳንን የስደት ሀገሩ አድርጎ ሲያበቃ፥ በሶማሊያና በሳውዲ አረብያ በአሜሪካ ጦር ኃይል ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ሲያቀነባብር የነበረው ከዚያ እንደነበር ይነገራል። ሱዳን በዩናይትድ ስቴትስ ጫና በሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ስድስት ቢን ላድንን ከአገርዋ አስወጣችው፥ እናም ለሁለተኛ ጊዜ ወደአፍጋኒስታን ተመልሶ ሄደ።
ቪክራም ፓሬኽ ቢሮው ብረሰልስ የሆነው ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ ተንታኝ ናቸው። ቢን ላድን ፈጥኖ የአዲሶቹ የአፍጋኒስታን መሪዎች አክራሪ እስላማዊ ታሊባን ንቅናቄ መሪዎች ጋር የቅርብ ወዳጅ ሆኖ በሚያስፈልጋቸው ገንዘብ ይረዳቸው ጀመር።
ቪክራም ፓሬኽ፥--
”ይህም ለታሊባን ሙሉ በሙሉ ለአስተዳደሩና ለወታደራዊ ዘመቻው ቅንብር ይተማመንባት ከነበረው ከፓኪስታን ነጻ የሆነ የገንዘብ ምንጭ ሰጠው ማለት ነው።”
ቢን ላድን እንደገና በአፍጋኒስታን ፖለቲካ ውስጥ ይሳተፍ እንጂ በጎን ደግሞ ዓለም አቀፍ ጸረ ዩናይትድ ስቴትስ ትግሉን ቀጠለ። በሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ስምንት በኬንያ እና በታንዜንያ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ የደረሱትን ጥቃቶች ያቀነባበረ እሱ እንደሆነ ነው የተነገረው።
የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ተንታኝ ቪክራም ፓሬኽ ሲያስረዱም ኦሳማ ቢን ላድን በምዕራባዊያን ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች ስሙ በተነሳ ቁጥር በተከፉ አረቦች ዘንድ ተወዳጅነቱ እየበረታ መጣ፥ ዩናይትድ ስቴትስ በመካከለኛው ምስራቅ የምትከተለውን ፖሊሲ በማይወዱም ዘንድ እንዲሁ።
ቪክራም ፓሬኽ አክለውም እንዲህ አሉ፣--
”ኦሳማን ሰዎች እንደግለሰብም ይሁን በርዕዩተ ዓለሙ ይውደዱትም አይውደዱትም ለዩናይትድ ስቴትስ ያለመበገር ተምሳሌት ሆኖ መታየት ጀመረ።”
በሁለት ሺህ አንድ በኒውዮርክ እና በዋሽንግተን ከሶስት ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ከገደሉት ጥቃቶች ተከትሎ ዩናይትድ እስቴትስ ቢን ላድንን ማስቆምን አንገጋቢ ትኩረትዋ አድርጋ ተነሳች።
ታሊባኖች የአልቃይዳውን መሪ ለዩናይትድ ስቴትስ ባለልጣናት ማስረከብን አሻፈረኝ በማለታቸው ዩናይትድ ስቴትስ ጦርነት ከፈተችና ታሊባኖቹን ሁለት ሺህ አንድ ታህሳስ ወር ላይ ከስልጣን አስወገደች፥ ቢንላድንም ያኔ ተሸሸገ።
በነዚህ ዓመታት ሁሉ ታዲያ ኦሳማ ቢን ላድን ከተደበቀበት ሆኖ በየጊዜው ዩናይትድ ስቴትእስ እያወገዘ ድምጹን ሲያሰማ እና ዋሽንግተንን እጅጉን ሲያናድድ ነው የኖረው። እነሆ ያ ዘመን ነው አሁን ያከተመው።
የኦሳማ ቢን ላድን አደን ገና እንዲህ ከመደምደሙ በፊትም የቀድሞ የሲ አይ ኤ የማዕከላዊ ስለላ ድርጅት የጸረ ሽብርተኛ ክፍል ሹም የነበሩት አምባሳደር ጄ ኮፈር ብላክ ዕለቱ በዩናይትድ ስቴትስ ለብዙዎች ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረው ተናግረው ነበር።
”ጥሩ ቀን! በርግጥም በመስከረም አንዱ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ቤተሰቦች ሁሉ የሚያስታውሱት ቀን!” ነበር ያሉት አምባሳደር ኮፈር ብላክ
ያም ሆኖ አሉ አምባሳደር ኮፈር ብላክ ያም ቢሆን ከባዕዳን ሽብርተኞች በዩናይትድ ስቴትስ ላይ የሚደቀነው ስጋት አከተመ ማለት አይደለም።


ዘገባውን ያዳምጡ

XS
SM
MD
LG