በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአልቃይዳው አሸባሪ ድርጅት መሥራችና መሪ ኦሳማ ቢን ላደን ተገደለ


ኦሳማ ቢን ላደን አልቃይዳ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር መስከረም 1 ቀን 2001 ዓ ም ባደረሳቸው ጥቃቶች ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎች ከተገደሉ ወዲህ በዓለም ቁጥር አንድ አሸባሪ ተብሎ ሲታደን ቆይቷል።

ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ የአሜሪካ ሕዝብ ለአሥር ዓመታት ግድም በከፍተኛ ትዕግስት ሲጠብቀው የቆየውን ዜና ትላንት ማታ ይፋ ያደረጉት በዋሺንግተን አቆጣጠር ከዕኩለ ሌሊት 25 ደቂቃዎች በፊት ነው።

«ዩናይትድ ስቴትስ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሐን ወንዶች፥ ሴቶችና ሕፃናት የፈጀውን የአልቃይዳውን መሪና አሸባሪ ኦሳማ ቢን ላደንን የገደለ ወታደራዊ እርምጃ መውሰዷን ለአሜሪካ ሕዝብና ለመላው ዓለም አሳውቃለሁ» ብለዋል ፕሬዘዳንቱ።

ኦሳማ ቢን ላደን አልቃይዳ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር መስከረም 1 ቀን 2001 ዓ ም ባደረሳቸው ጥቃቶች ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎች ከተገደሉ ወዲህ በዓለም ቁጥር አንድ አሸባሪ ተብሎ ሲታደን ቆይቷል።

ፕሬዘዳንት ኦባማ በትላንት ምሽቱ መግለጫቸው ቢን ላደን ወደተሸሸገበት ሥፍራ ሊያመራ የሚችል ጥቆማ መኖሩ የተገለጸላቸው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ውስጥ እንደሆነና የአሸባሪው ድርጅት መሪ ተሸሽጐ የሚገኘውም ፓኪስታን ውስጥ አቦታባድ እየተባለ በሚጠራ ሥፍራ አንድ ግቢ ውስጥ መሆኑ የተብራራላቸው እንደሆነ አስረድተዋል።

ያ መረጃ ከተገኘ ከበርካታ ወራትና ጉዳዩ በከፍተኛ ሚስጥርነት ተጠብቆ ክትትሉ ከቀጠለ በኋላ፥ ኦሳማ ቢን ላደን ተይዞ ለፍርድ እንዲቀርብ የሚያስችል ተልኰ እንዲፈጸም ሚስተር ኦባማ ትዕዛዙን የሰጡት ባለፈው ሣምንት መሆኑንም አብራርተዋል። በዚሁ ትዕዛዝ መሠረትም አነስተኛ ቁጥር ያለው ያሜሪካ ወታደራዊ ቡድን ትላንት ዕሁድ ያሸባሪዎቹ መሪ በተሸሸገበት ቅጽር ግቢ ላይ ዘመቻውን አካሂዷል ብለዋል።

«በግቢው ውስጥ የተኩስ ልውውጥ ከተካሄደ በኋላ ኦሳማ ቢን ላደንን ገድለው አስከሬኑን በቁጥጥር ሥር አድርገዋል» ሲሉም አስረድተዋል።

አልቃይዳ በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ጥቃት ማድረሱን ሊቀጥል እንደሚችል ፕሬዘዳንቱ አረጋግጠው፥ አሜሪካውያን አሁንም ነቅተው እንዲጠባበቁ አስገንዝበዋል።

«ፕሬዘዳንት ቡሽ ከመስከረም አንዱ ጥቃት ጥቂት ጊዜ በኋላ እንደገለጹት ሁሉ፥ ጦርነት የያዝነው ከእስልምና ጋር አለመሆኑን ግልፅ አድርጌአለሁ። ምክንያቱም ኦሳማ ቢን ላደን የሙስሊሞች መሪ አልነበረምና ነው። ይልቅስ ሙስሊሞችን በገፍ የፈጀ አሸባሪ ነው። በእርግጥም አልቃይዳ የእኛን ጨምሮ በበርካታ ሀገሮች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሙስሊሞች አርዷል» ብለዋል ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ በትላንቱ ንግግራቸው።


ዝርዝሩን ያድምጡ።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG