ኦሳማ ቢን ላድን በአፍሪካ ላይ ካነጣጠራቸው የሽብር ስራዎች፣ ብዙ ሰዎችን የገደለው በ1990 ዓም በኬንያና ታንዛንያ የሚገኙ የዩናይትድ ስቴይትስ ኢምባሲዎች የደረሰው ፍንዳታ ነው።
በጥቃቱ 224 ሰዎች ተገድለዋል።
የኬንያ ፕሬዝደንት ምዋይ ኪባኪ የኦሳማ ቢን ላድንን በአሜሪካ ልዩ ሃይሎች መገደልን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት “ፍትህ ሚዛኗን አደላደለች” ሲሉ ተናግረዋል።
በናይሮቢ ቦምብ ጥቃት ላይ የተባበሩን ሁሉ የሚይዙ መንግስታትን ፕሬዝደንት ኪባኪ አወድሰዋል።
ባለፈው ሳምንት በአልቃይዳ ከፍተኛ ጥቃት የደረሰባት ሞሮኮ ደግሞ የማስታወቂያ ሚኒስትር ኻሊድ ናችሪ በቢን ላድንና በድርጅቱ ያልተነካ የአለማችን ክፍል አይገኝም ብለዋል።
ናችሪ አክለውም የሞሮኮ ህዝብ በንጹሃን ግድያ የማያምን መሆኑንና ሁከት ፈላጊነትን አገሪቱ አጥብቃ እንደምታወግዝ ገልጸዋል።
የደብቡ አፍሪካ መንግስት ደግሞ ጥንቃቄ የተመላበት መግለጫ አውጥቷል። ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ዜናውን ለአለም ህዝብ ይፋ ካደረጉ በኋላ የደቡብ አፍሪካ መንግስት በአጭሩና በደፈናው “ምንም አይነት የሽብርተኝነት ተግባርን በምንም አይነት ገጹ እንደማይቀበለው” የውጭ ጉዳዮችና ትብብር ሚኒስቴር አስታውቋል። ይሄንንም ለመታገል አለም አቀፍ ስምምነትና ትብብር ሊኖር እንደሚገባም አሳስቧል።
በናይጀሪያ የደህንነት ማካሪ የሆነው ኢቫወሬ ኦይዴ በኦሳማ ቢን ላድን ግድያ አፍሪካዊያን ያላቸው ምላሽ የተዘበራረቀ ነው ይላል።
“አንዳንድ ሰዎች ይሄንን እንደ እፎይታ ይመለከቱታል። ሌሎች ደግሞ ምእራባዊያንን አጥብቆ የሚቃወምና የሚዋጋ ሰው ብለው ያስቡታል። ለብዙ ሰዎች ኦሳማ ጀግናቸው ነው። አሜሪካ ባላት የደህንነትና የወታደራዊ አቅም ለአስር አመት ልትይዘው ያልቻለች ሰው ነው በሚል ያደንቁታል።”
በናይጀሪያ በንግድ የሚተዳደረው አንድሩ ኢጂሮ ክሮስ ደግሞ ኦሳማ ቢን ላድን መገደል አልነበረበትም ይላል። እንዲያውም ትጥቁን አስፈትተው እጁን ይዞ የኦባማ አስተዳድር ለፍርድ ሊያቀርበው ይገባ ነበር ይላል። ከሶቪየት ህብርት ጋር ባደረጉት ጦርነት ኦሳማን ለዚህ እንዲበቃ የደገፉት አሜሪካኖቹ እራሳቸው ናቸው ይላል ክሮስ፤ በዚህም አሜሪካን ተጠያቂ ያደርጋል።
“ኦሳማ ቢን ላድን ገንዘብ ይፈልግ የነበረ ነጋዴ ነበር። አሜሪካኖቹ ተጠቀሙበት። የፈለጉትን ካደረጉ በኋላ አሁን ደግሞ ገደሉት። መግደሉ ለምን አስፈለገ? አሜሪካ ከጠላችህ በቃ አለቀልህ፤ ይገድሉሃል።”
የዩጋንዳ መንግስት በበኩሉ የኦሳማን መገደል “የምስራች” ብሎታል። የመንግስቱ ቃል አቀባይ ፍሬድ ኦፖሎት በሶማሊያ በሰላም ማስከበር ስራ የተሰማሩ የዩጋንዳ ወታደሮች ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አላቸው ያሉትን አል-ሸባብን በርትተው እንዲዋጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው አልሸባብ የኦሳማ ቢን ላድንን ደም እንደሚበቀል አንድ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ተናግረዋል። የኬንያ መንግስት የደህንነት ጥበቃውን ማጠናከሩንና በተለይ ከሶማሊያ ጋር በሚዋሰነው ግዛቱ ስጋቱ የጠነከረ ስጋት እምዳለው መንግስቱ አስታውቋል።