በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳትን ሾመች


በብፁዕ ወቅዱስ አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
በብፁዕ ወቅዱስ አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ትላንት እሑድ፣ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በዐዲስ አበባ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም፣ በብፁዕ ወቅዱስ አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ እጅ መጫን፣ ኤጲስ ቆጶስነት የተሾሙት ዘጠኙ አባቶች፣ በዘጠኝ አህጉረ ስብከት ላይ በአባትነት መመደባቸው ታውቋል፡፡

ክፍት በኾኑ፣ በተደራቢነት በተያዙና አንገብጋቢ ችግር ባለባቸው ሰባት የኦሮሚያ ክልል እና ሁለት የደቡብ ኢትዮጵያ አህጉረ ስብከት የተሾሙት ኤጲስ ቆጶሳቱ፣ “ከዛሬ ጀምሮ ዘመድ አዝማድን፣ ብሔርንና ዘውግን፣ ቤተሰብንና ሀብትን ብቻ ሳይኾን፣ ራሳቸውንም ክደው” አገልግሎታቸውን ያለአድልዎ እንዲፈጽሙ ከፓትርያርኩ አደራን ተቀብለዋል፡፡

ኦርቶዶክሳዊው ሕዝበ ክርስቲያን ባቀረበው አቤቱታ፣ የተፈጸመው የቀኖና ጥሰት ታርሞ፣ በዛሬው ዕለት ትክክለኛውን ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንና ቀኖናዊ ሕግን ጠብቀን ሥርዐተ ሢመቱን በማከናወናችን፣ ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን እንኳን ደስ አላችኹ፤”

ኤጲስ ቆጶሳቱ ለሹመቱ የተመረጡት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በግንቦቱ መደበኛ ስብሰባው በሠየመው አስመራጭ ኮሚቴ ተመልምለው ከቀረቡ በኋላ ነው፡፡ የምርጫ መስፈርቱ፥ መንፈሳዊ ንጽሕናንና የአገልግሎት ብቃትን ሳይኾን የብሔር ማንነትን መሠረት አድርጎ ያለካህናት እና ምእመናን ተሳትፎ በከፍተኛ ምስጢር መከናወኑ፣ ከእምነቱ ተከታዮች ዓለም አቀፍ ትችትን እያስተናገደ ይገኛል፡፡

ይህም ኾኖ ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ በበዓለ ሢመቱ ላይ ባስተላለፉት ምዕዳንና ቡራኬ፣ “ኦርቶዶክሳዊው ሕዝበ ክርስቲያን ባቀረበው አቤቱታ፣ የተፈጸመው የቀኖና ጥሰት ታርሞ፣ በዛሬው ዕለት ትክክለኛውን ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንና ቀኖናዊ ሕግን ጠብቀን ሥርዐተ ሢመቱን በማከናወናችን፣ ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን እንኳን ደስ አላችኹ፤” ሲሉ መልዕክት ማስተላለፋቸውን የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ዘግቧል፡፡

የትላንቱ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት የተፈጸመው፣ ባለፈው ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ - ወሊሶ ሀገረ ስብከት ሀሮ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን፣ በሦስት ሊቃነ ጳጳሳት በድብቅ የተካሔደው የ26 መነኰሳት ሹመት፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ ከተወገዘና ሰፊ ተቃውሞ ማስነሣቱን ተከትሎ፣ የተጣሰውን ቀኖና በቀኖናው ማረም አስገዳጅ ኾኖ በመገኘቱ እንደኾነ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተናግረዋል፡፡

ፓትርያርኩ አያይዘውም፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ባልተጠበቀና ባልተለመደ ኹኔታ ብቅ ብቅ ሲሉ የሚታዩት፣ ራስን በራስ የመሾም አባዜ መገታት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ይልቁንም፣ ማንኛውም ችግር፣ በውይይት እና በምክክር የተበደለውንም በትክክል በመካስ መፈታት እንደሚኖርበት አመልክተዋል፡፡

በትግራይ ክልል የሚገኙ የአራት አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት፣ 10 ኤጲስ ቆጶሳትን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ለመሾም፣ ትላንት የተሿሚ ቆሞሳትን ምርጫ በአኵስም ያካሔዱ ሲኾን፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በበኩሉ፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ያልተከተለ እንደኾነና የሚመለከታቸው አካላት ሒደቱን በማስቆም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጎን እንዲቆሙ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ሕገ ወጥ ነው ለተባለው ምርጫ እና ሹመት መነሻ ለኾነውና ጦርነቱን ተከትሎ ለተፈጠረው የትግራይ አህጉረ ስብከት ብፁዓን አባቶች ቅሬታ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ይቅርታ ቢጠይቅም፣ አዎንታዊ ምላሽ አለመሰጠቱ በእጅጉ እንዳሳዘነው ቅዱስ ሲኖዶስ ገልጿል፡፡

በቅዱስነታቸው የሚመራ 21 አባላት ያሉት የሰላም ልኡክ፣ ባለፈው ሐምሌ 3 ቀን፣ ወደ መቐለ በማቅናት በጊዜያዊ አስተዳደሩ አመቻችነት ከአራቱ የአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት እና የሥራ ሓላፊዎች ጋራ ለመወያየት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለት አስታውቋል፡፡ ኾኖም፣ ለሰላም የሚያደርገውን ጥረት እንደሚቀጥልና ይህንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የክልሉ የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት፣ መንግሥታዊ እገዛ በማድረግ የውይይት መድረክ እንዲያመቻቹ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG