የኦፌዴን ፀሐፊ አቶ በቀለ ነጋ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃል በፓርቲያቸው አባላት ላይ ቀደም ሲል የተለያዩ የማንገላታትና የእሥራት በደሎች የፈፀሙባቸው እንደነበር አስታውሰው ከ2002 ዓ.ም ሃገር አቀፍ ምርጫ በኋላ ግን ኦፌዴን በሚንቀሣቀስባቸው አካባቢዎች ይህ በአባሎቻቸው ላይ ይፈፀምባቸው የነበረው ማዋከብ ረገብ ብሎ እንደቆየ አቶ በቀለ ገልፀዋል፡፡
በያዝነው መጋቢት ውስጥ ግን "እንግልትና ወከባው አገርሽቶበታል" የሚሉት አቶ በቀለ ነጋ ምሣሌ ሲጠቅሱ በቄለም ወለጋ በምርጫ 2002 ታዛቢ የነበሩ አቶ ኢታና ሰንበቶ የሚባሉ የድርጅታቸው አባል መኖሪያ ቤት መጋቢት 4 ሌሊት በታጣቂዎች ተከብቦና ተፈትሾ ከተያዙ በኋላ "ያልታወቀ" ወዳሉት አካባቢ መወሰዳቸውን ቤተሰቦቻቸው የነገሯቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም በምዕራብ ወለጋም በጊምቢ ዞን ባለፈው ምርጫ ለፓርላማ የተወዳደሩ አቶ ሙላቱ ሺፈራው የሚባሉ አባላቸው እቤታቸው ድረስ ሄደው ፈልገው ስላላገኟቸው የአሥራ አራትና የአሥራ አምስት ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ደበላ ሙላቱና ሃብታሙ ሙላቱ የሚባሉ ሕፃናት ልጆቻቸው ተወስደው መታሠራቸውን ገልፀዋል፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ ፅ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ኦልባና ሌሊሣም በእርሣቸው ፓርቲም ላይ ተመሣሣይ አድርጎቶች መፈፀማቸውን አስታውቀዋል፡፡
እሥራት የሚካሄድባቸው እጅግ ስፋት ያላቸው አካባቢዎችና የሕብረተብ ክፍሎችን የሚያካትቱ መሆናቸውን አቶ ኦልባና ገልፀው በሦስትና በአራት ቀናት ውስጥ ወደ ሃያ አራት ሰው መታሠሩን አመልክተዋል፡፡
ታሣሪዎቹ ተጠርጥረዋል የሚባሉባቸው የወንጀል ዓይነቶች፣ "የጦር መሣሪያ ገዝቶ አጠራቅሟል፤ ሕዝብን የሚያነሣሱ ወረቀቶችን ለመበተን ተዘጋጅቷል፤ በሽብር ወንጀል ተጠርጥሯል፤" የሚሉ መሆናቸውን አቶ ኦልባና አክለው ገልፀዋል፡፡
"ታሠሩ" ከተባሉት የኦሕኮ አባላትና ደጋፊዎች መካከል አቶ ጉቱ ሙሊሣ የሚባሉ ሰው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይዘዋል በተባሉ ፖሊሶች ከሌሊቱ በዘጠኝ ሰዓት መኖሪያ ቤታቸው ተከብቦ መያዛቸውን ባለቤታቸው ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከዚህ በፊትም አባሎቻቸው በተደጋጋሚ እንደሚታሠሩባቸውና እንግልትም እንደሚደርስባቸው ሲያማርሩ ቆይተዋል፡፡
መንግሥት በበኩሉ ሰዎቹ የሚታሠሩት የፓርቲ አባል ስለሆኑ ሳይሆን ወንጀል በመፈፀማቸው ነው ይላል፡፡
ለዝርዝርና ለተጨማሪ መረጃ ዘገባውን ያዳምጡ።