ዋሽንግተን ዲሲ —
የጨፌ ኦሮሚያ መቀመጫ በሆነችው አዳማ በተጠራው ሰልፍ ላይ የከተማይቱ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የአካባቢው ከተሞች ነዋሪዎች፣ ኦሮሞዎች ብቻ ሣይሆኑ የሌሎችም ማኅበረሰብ ክፍሎች አባላት ሁሉ እንዲገኙና ለጥያቄዎቹ ድጋፍ እንዲሠጡ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ የምሥራቅ ሸዋ ዞን አመራር አባል ኦቦ ቦና ገዳ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኦቦ ቦና ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ጥያቄዎቻቸው ኦፌኮ ሰሞኑን ባወጣው ባለአሥር ነጥብ መግለጫ ውስጥ የተካተቱ መሆናቸውን አመልክተው ከእነዚህ ውስጥም “ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እያቀረቡ ባሉ የኦሮሚያ ተማሪዎች ላይ እየተካሄደ ያለው ድብደባ፣ እሥራትና ግድያ ይቁም፤ የአዲስ አበባን ማስተር ፕላንና የኦሮሚያን የከተሞች አዋጅ እንቃወማለን” የሚሉ እንደሚገኙበት አስታውቀዋል፡፡
የአዳማው ሰልፍ ቅዳሜ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ከመስቀል አደባባይ ተነስቶ ወደ ጨፌ ኦሮሚያ ጉዞ እንደሚደረግ አቶ ቦና ተናግረዋል፡፡
ከአዳማው ሰልፍ በተጨማሪ በቡራዩ፣ በሰበታ፣ በሱሉልታና በነቀምትም ተመሣሣይ ሠልፎች መዘጋጀታቸውን የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ ዋና ፀሐፊ አቶ በቀለ ነጋ ለቪኦኤ ገልፀዋል፡፡
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡