የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ተግባራዊ ይደረጋል መባሉን ተከትሎ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በኋላ እንደገና ያገረሸው ተቃውሞ ለአራተኛ ሣምንት ዛሬም ቀጥሎ ውሏል፡፡
የማስተር ፕላኑ ዕቅድ በወጣበት በግንቦት ወር 2006 ዓ.ም ወቅትም እንዲሁ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሶ እንደነበር የሚታወቅ ሲኾን በወቅቱም የሰዎች ሕይወት ማለፉ፣በርካቶች መቁሰላችውና መታሰራቸው ሲዘገብ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የኦሮሚያ ክልል እና የፌደራል ባለሥልጣናት ማስተር ፕላኑ የሕዝብ ይሁንታን ካላገኘ ተግባራዊ እንደማይደረግ በመግለጻቸው ኹኔታዎቸ የተረጋጉ መስለው ነበር፡፡
ከአራት ሣምንት በፊት ግን በምዕራብ ሸዋ ዞን ዶንዲ ወረዳ የሚገኘው ጪሊሞ ደን ለግለሰብ መሸጡን በመግለጽ እንዲሁም በዚሁ ወረዳ ለሚገኘው ጊኒጪ ትምሕርት ቤት የተሰጠውን የማስፋፊያ ቦታ የካቢኔ አባላት ተከፋፍለውታል በማለት ተቃውሟቸውን ማሰማት ጀምሩ። በተጨማሪም ማስተር ፕላኑም ባይጸድቅ የኦሮሚያ ከተሞች ማሻሻያ ዐዋጅ በክልሉ ምክር ቤት ማለትም በጨፌ ኦሮሚያ በኩል መፅደቁ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ የተዳፈነውን ተቃዉሞ እንደገና ቀስቅሶታል፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥ በአብዛኛው የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ተቃውሞውም እየተዛመተ ሄዶ፣ በሌሎች የኦሮሚያ ከከተሞች፣አሁን ደግሞ በወረዳ እና በቀበሌዎች ቀጥሏል፡፡ በዚህም መንግሥት የሞተው አምስት ሰው እንደኾነ ገልጿል፡፡ በዛሬው ዕለት መግለዐጫ የሰጠው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ሟቾቹን በስም ጠቅሶ 32 ሰው መገደሉን አስታውቋል፡፡ ጉዳዩን በቅርብ ሲከታተሉ የቆዩት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ዋና ጸሐፊ አቶ በቀለ ነጋ ስለሟቾቹ ማንነት ማስረጃ እንዳላቸው በመግለጽ የሟቾች ቁጥር እስከ ትላንት ድረስ አርባ መድረሱን ይናገራሉ፡፡ዛሬስ?
ጽዮን ግርማ ያጠናከረችውን ሙሉ ዘገባ ከተያያዘው ድምጽ ያድምጡ፡፡