በዶክተር መረራ ጉዲና የሚመራው የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስና፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አመራርና አባላት የሽብርተኛ ድርጅት አላማን ለማሳካት አሲራችኋል በሚል ለቀረበባቸው ክስ በፍርድ ቤት ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ተከራክረዋል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰኞለት ባስቻለው ችሎት የየኦሮሚ ህዝብ ኮንግረስ (ኦሕኮ) ጸሃፊ አቶ ኦልባና ሌሊሳና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) የክስ መዝገብ፤ በዘጠኝ ተከሳሾች ላይ የቀረበውን ክስ አዳምጧል።
በትጥቅ ትግል የኢትዮጵያን መንግስት ለመጣል ወይንም ኦሮሚያን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የሚዋጋው የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን አላማ በድብቅ ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ ተይዘዋል ይላል የአቃቢ ህግ ክስ።
እነዚህ ሰዎች ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በሽፋንነት በመጠቀም መንግስትን በሃይል ለመጣል አሲረዋል፣ በትጥቅ ትግል የኦሮሚያን ክልል ከፌዴሬሽኑ እንገነጥላለን ሲሉ አሲረዋል ሲል አቃቢ ህግ ክሱን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
የኢትዮጵያን የፖለቲካና የግዛት አንድነት ተጻረዋል ይላል ክሱ።
ተከሳሾች እነዚህን ክሶች መፈጸም አለመፈጸማቸውን የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ በፍርድ ቤቱ ሲጠየቁ፤ የኦፌዴኑ አቶ ኦልባና ሌሊሳ የኦሮሚያ ህዝብ የሚደርስበትን ጭቆና በሰላማዊና በህጋዊ መልኩ እንደሚታገሉ ተናግረዋል።
በቀጥታ ጥያቄውን እንዲመልሱ በተጠየቁት መሰረት አቶ ኦልባናና ሌሎቹ ተከሳሾችም የቀረቡትን ወንጀሎች እንዳልፈጸሙ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
ተጨማሪ የምስክሮችን ቃል ለመስማት ፍርድ ቤቱ በነገውለት ያስችላል።