በመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች እና በኦሮሞ ነጻነት ታጣቂዎች መካከል የቀጠለው ግጭት እንዲቆም የሚጠይቁ ሰልፎችን ያካሔዱ፣ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ነዋሪዎች፣ “የአካባቢው ባለሥልጣናት ጣልቃ እየገቡ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዓላማቸው አንዱን ቡድን ደግፎ ሌላውን ማውገዝ እንዳልኾነ የገለጹት እነዚኽ አስተያየት ሰጭዎች፣ የወረዳ እና የዞን ባለሥልጣናት ግን፣ “ሰልፉ በመንግሥት የተዘጋጀ ለማስመሰል እየሞከሩ ነው፤” በማለት ወቅሰዋል።
እየተደረጉ ያሉትን ሰልፎች “እናበረታታለን” ያሉት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቃል አቀባይ ኀይሉ አዱኛ፣ “የመንግሥት አካላት ጣልቃ እየገቡ ነው” መባሉን ግን አስተባብለዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ያያ ጉለሌ ወረዳ ፊታል ከተማ ነዋሪ የኾኑትና በደኅንነት ስጋት ምክንያት ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ የሰላም ጥሪው ሰልፍ ተሳታፊ፣ በዞኑ ባሉት ወረዳዎች ውስጥ ከአምስት ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ በገለጹት የጸጥታ ችግር ሳቢያ፣ የጤና፣ የትምህርት እና የመሳሰሉት ተቋማት አገልግሎት እንደተቋረጡ መኾናቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
በተለይ በገጠር ቀበሌዎች ውስጥ፣ “አርሶ አደሮች ማሳቸውን ለማረስ እንኳን አልቻሉም፤” ያሉት እኚሁ ነዋሪ፣ “ሕይወቱ የተመሰቃቀለበት ሕዝብ፣ መፍትሔ አገኝ ይኾን በሚል በሃይማኖታዊ መንገድ እግዚኦታን ለማቅረብ ሰልፍ ወጥቷል፤” ብለዋል፡፡
ሰላማዊ ሰልፉን የማካሔድ ተነሣሽነት የራሱ የሕዝቡ መኾኑን ነዋሪው ገልጸዋል፡፡ ዓላማውን በተመለከተ ሲያስረዱም፣ “መንግሥትም ኾነ ታጣቂው ቡድን፣ ችግራችንን ተረድተው ወደ ሰላም እንዲመጡና ሰላም እንዲወርድ፤ ሕዝቡ በጸጥታው ችግር ሳቢያ በረኀብ እንዳያልቅ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፣ ሕይወቱ በየሜዳው እንዳያልፍ ለመማፀን ነበር፤” ብለዋል፡፡
ኾኖም፣ የወረዳዎች እና የዞኑ የመንግሥት መዋቅሮች፣ “ሐሳባችንን ነጠቁን፤ የራሳቸው አስመስለው የታጣቂውን ቡድን ብቻ ለማውገዝ የወጣን አስመሰሉን፤” ሲሉ ወቅሰዋል አስተያየት ሰጪው፡፡ አያይዘውም፣ “የእኛ ጥሪ ለሁለቱም ነበር፤ ነገር ግን መልዕክታችንን ባሰብነው መንገድ ማሰማት አልቻልንም፤” በማለት ወቀሳቸውን አጠናክረዋል፡፡
የጫንጮ ወረዳ ነዋሪ መኾናቸውን የገለጹትና በተመሳሳይ የደኅንነት ስጋት ምክንያት ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁት ሌላ ነዋሪም፣ “አባገዳዎች፣ ሀደ ስንቄዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተውበታል፤” ባሉት በዚኹ ሰልፍ፣ መንግሥትም ኾነ ታጣቂው ቡድን ወደ ሰላም እንዲመጡ መማፀናቸውን ተናግረዋል፡፡
“እኛ፥ ጥማድ በሬ፣ ፈረስ፣ ጫጩት፣ ከለቻ ይዘን የወጣነው፥ ችግሮች ስለተፈራረቁብን፣ ሰው ካልሰማን ፈጣሪ ይስማን ብለን ነበር፤” ያሉት እኚኹ ነዋሪ፣ ከሰልፉ ጋራ በተያያዘ፣ “የመንግሥት ሹመኞች እና ደጋፊዎች” ባሏቸው ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ “ሕዝቡ በአዘጋጀው ፕሮግራም ላይ፣ የመንግሥት ሹመኞች እና ደጋፊዎች እየተገኙ ራሳቸው ያዘጋጁት በማስመሰል የራሳቸውን መልእክት አስተላልፈዋል፤” በማለት አካሔዱ አግባብነት እንደሌለው ተችተዋል፡፡
“ይህ እግዚኦታ ለሦስት ዙር ነው የሚካሔደው፤ ይቀጥላል፤” ሲሉም አመልክተዋል፡፡
ነዋሪዎቹ፣ የሰላም ጥሪ ባስተላለፉበት ሰልፍ፥ “የመንግሥት መዋቅሮች ጣልቃ ገብተውብናል፤” ሲሉ ያቀረቡትን አቤቱታ በተመለከተ ምላሽ የተጠየቁት የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ሓላፊ አቶ ኀይሉ አዱኛ፣ ሰልፉን ያዘጋጀው ሕዝቡ ራሱ መኾኑን አረጋግጠው፣ “ባለሥልጣናት ጣልቃ እየገቡ ነው፤” የሚለውን ወቀሳ ደግሞ አስተባብለዋል።
ይህ ዓይነቱን ጥሪ፣ ከዚኽ በፊትም መንግሥት በተደጋጋሚ ሲያስተላልፍ እንደነበር አቶ ኀይሉ አውስተው፣ የሰላም ዕንቅፋት የኾነው፣ “ሸኔ” ሲሉ የጠሩት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንጂ መንግሥት አይደለም፤ ሲሉ ከሰዋል፡፡ አሁንም፣ ሕዝቡ በሰላማዊ ሰልፍ ያቀረበውን የሰላም ጥሪም መንግሥት እንደሚደገፍ አስረድተዋል።
በአንጻሩ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ከዚኽ ቀደም ለቀረቡበት ተመሳሳይ ውንጀላዎች በሰጠው ምላሽ፣ ለጸጥታው ችግር መንግሥትን ተጠያቂ ማድረጉ አይዘነጋም።
መድረክ / ፎረም