በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሥርዓተ-አልበኝነትን ለማስወገድ እየሠሩ መሆናቸውን ለማ መገርሣ አስታወቁ


ለማ መገርሳ
ለማ መገርሳ

ኦሮምያ ውስጥ አልፎ አልፎ ይታያል ያሉትን የሥርዓተ-አልበኝነት ችግር ለማስወገድ ከሕዝብ ጋር ሆነው እንደሚሠሩ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ለማ መገርሣ አስታውቀዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ኦሮምያና ሶማሌ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ላይ ሲነሱ በቆዩ ግጭቶች ምክንያት ኦሮምያ ውስጥ 159 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ቶላ በሪሶ ለቪኦኤ ገልፀዋል።

የፀጥታ ችግር ሥጋት ወደ አማራ ክልል እንዲሸሹ ያደረጋቸውን ምዕራብ ኦሮምያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የአማራ ተወላጆችን በአጭር ጊዜ ውስጥ መልሰን ለማቋቋም ዝግጅት አጠናቅቀናል ብለዋል የኦሮምያው ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሣ።

“የመልካም አስተዳደር መጥፋት ከኪራይ ሰብሳቢነትና ከጎሰኛነት ጋር ተያይዘው እታች ያለ ሥልጣንን በመጠቀም ሲፈጠር በነበረው የአስተዳደር ችግር ላይ የማስተካከያ እርምጃዎች ተወስደዋል። ስለዚህ ከአሁን በኋላ በጉባዔአችን ላይ የተላለፉ ውሣኔዎችን ተመርኩዘን ከታች ወይም ከዝቅተኛው ደረጃ ጀምሮ በሙሉ አቅም እንሠራለን” ብለዋል።

አክለውም በምዕራብ ኦሮምያ በግለሰብ ደረጃ በተፈጠሩ ግጭቶችና የፀጥታ ችግር ፍራቻ የአማራ ተወላጆች መፈናቀላቸውንና መሸሻቸውን አስመልክቶ አቶ ለማ ሲናገሩ “እነዚህ የተፈናቀሉ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ የክልላችን ነዋሪዎች እስከሆኑ ድረስ የመኖር መብት ስላላቸው ሁኔታው ተጠንቶ ይኖሩባቸው ወደነበሩ ቀዬዎቻቸው እንዲመለሱ ዝግጅት ተጠናቅቋል። በኦሮምያ ክልላዊ መስተዳደር በኩል አስፈላጊ የሆኑ ሁኔታዎች ተመቻችተው ይህንን የሚያስፈፅም አካልም ተሰይሞ ሥራ ጀምሯል” ብለዋል።

በኦሮምያ ክልል በጉጂና በደቡብ ክልል በጌዴዖ ዞኖች አዋሣኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት ለማስቆም ያለማቋረጥ እየተሠራ መሆኑን አቶ ለማ ገልፀዋል።

የተፈናቀሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደመኖሪያቸው እንደሚመለሱና ለግጭቶቹ መጫር ምክንያት የሆኑ ሕግ ፊት እንደሚቀርቡ ጠቁመው ተመሣሣይ ችግር ወደፊት እንዳይፈጠር ሕዝቡ ከጎናቸው እንዲቆምና አብሯቸው እንዲሠራ ጥሪ አሰምተዋል።

ኦሮምያ ውስጥ ከሚካሄደው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ እየጠየቁ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል የክልሉ ፕሬዚዳንት፤ “ከአመራር ጋር ተቀምጠው መነጋገር ያስፈልጋቸዋል። ኢንዱስትሪ ውስጥ የፀጥታ፣ የደመወዝና ሌሎችም ጉዳዮችን በተመለከተ የሚታዩ ክፍተቶች አሉ። ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም ለሠራተኛ የሚከፈል ወለል ወይም መነሻ ደመወዝ በጊዜው ተጠንቶ መቅረብ ስላልቻለ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸው ችግሮች አሉ። ጥሩ ያልሆነው ነገር ግን ከዚያ አልፎ የፋብሪካ ሠራተኞቻችንን፣ ባለሃብቶቻችንን፣ የሌሎች ሃገሮችን ዜጎች መደብደብ፣ መዝረፍና ማወክን የመሳሰሉ ሕገወጥ አድራጎቶች እየተስተዋሉ ነው። ይህ ደግሞ በብዙ መንገድ ይጎዳናል። መወያየት ያስፈልጋል። መብት መከበር አለበት” ብለዋል።

የኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሣ አክለውም - በራሣቸው አባባል - በሦስተኛ ወገን የሚቀርቡ አጀንዳዎች የሚሰጡንን ለይተን በማየት መብታችንን እያስከበርን ሥርዓተ አልበኝነትን ተባብረን በመጠበቅ ክልላችንን እና ሃገራችንን በሥርዓት መምራት አለብን” ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኦሮምያና ሶማሌ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ላይ ሲነሱ በቆዩ ግጭቶች ምክንያት ኦሮምያ ውስጥ 159 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ቶላ በሪሶ ለቪኦኤ ገልፀዋል።

ትምህርት ቤቶቹ አንድም ተዘግተዋል፤ ወይም ተዘርፈዋል፤ አልያም ጉዳት ደርሶባቸዋል - በክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ቶላ በሪሶ መግለጫ መሠረት።

በደረሰው ጉዳት ባለፈው ዓመት ከጂግጂጋ ከነቤተሰቦቻቸው የተፈናቀሉት የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎችን ጨምሮ ስድሣ ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መስተጓጎላቸውን ዶ/ር ቶላ አመልክተዋል።

በምሥራቅ ሃረርጌና ምዕራብ ሃረርጌ፣ ቦረና፣ ባሌና ጉጂ ዞኖች ውስጥ 159 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውንና መዘረፋቸውን የገለፁት ዶ/ር ቶላ በገንዘብ ሲተመን የ43.3 ሚሊዮን ብር ጉዳት እንደደረሰባቸውና አሁንም ከጂግጂጋ ከተፈናቀሉት መካከል 22 ሺህ ህፃናት አለመመዝገባቸውን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት እያደረገ ነው ባሉት ጥረት ተማሪዎቹ በየአቅራቢያቸው ወደሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተልከው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መደረጉን ዶ/ር ቶላ ገልፀዋል።

በዚህም ምክንያት በአንድ ክፍል ውስጥ የሚቀመጡ ተማሪዎች ቁጥር ከአርባ አምስት ወደ ሰባ እና ሰማንያ ማሻቀቡንም አስታውቀዋል።

ባለፈው ዓመት ከጂግጂጋ የተፈናቀሉ መምህራንን አስመልክቶም መንግሥታቸው እያደረገ ስላለው ጥረት የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“ከጂግጂጋ የተፈናቀሉ 437 መምህራንም ኦሮምያ ክልል ውስጥ በሚገኑ ትምህርት ቤቶች ተመድበዋል። በተጨማሪም ህፃናቱ ከትምህርታቸው እንዳይጨናገፉ መንግሥት ባደረገው ጥረት ተማሪዎቹን በየሚማሩበት እየመገበና አስፈላጊ የመማር ማስተማር ቁሣቁስ እና ግብዓቶችንም እያቀረበ ነው። የተዘጉትን ትምህርት ቤቶች ለመክፈትም ጥረት እየተደረገ ነው” ብለዋል።

በሶማሌ ልዩ ፖሊስ ይደርስባቸዋል በሚባለው ጥቃት በምሥራቅ ሃረርጌዋ ጭናቅሰን ወረዳ ሃያ ሰባት፣ በቦረና ዞኗ ሞያሌ አምስት፣ በጉጂ ዞኗ ጉሚ ኤልዳሎ ስድስት፣ በባሌ ሳወና አራት ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ብዙ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ማቋረጣቸውን ነው ኃላፊዎችና ነዋሪዎችም የሚናገሩት።

የተዘጉና አገልግሎት ያቋረጡ ትምህርት ቤቶች አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ ቤተሰቦች በግጭቶቹና በጥቃቶቹ ምክንያት በመፈናቀላቸው ሌሎች የልማት እንቅስቃሴዎችም መቋረጣቸውን ቪኦኤ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች አመልክተዋል።

የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

ሥርዓተ-አልበኝነትን ለማስወገድ እየሠሩ መሆናቸውን ለማ መገርሣ አስታወቁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:43 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG