በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኦሮሚያ ክልል የሰዴን ሶዶ ወረዳ አስተዳዳሪ በታጣቂዎች ተገደሉ


በኦሮሚያ ክልል የሰዴን ሶዶ ወረዳ አስተዳዳሪ በታጣቂዎች ተገደሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:22 0:00

በኦሮሚያ ክልል የሰዴን ሶዶ ወረዳ አስተዳዳሪ በታጣቂዎች ተገደሉ

በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ የሰዴን ሶዶ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በቀለ ቃቻ፣ ባለፈው ማክሰኞ፣ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች እንደተገደሉ፣ የወረዳው ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ)፣ ስለ ግድያው መረጃው ቢደርሰውም፣ በቦታው ተገኝቶ ማጣራት አለመቻሉን ገልጿል።

በኦሮሚያ ክልል፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ የሰዴን ሶዶ ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ በቀለ ቃቻ፣ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን ያስታወቀው፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ነው።

የዞኑ ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት፣ በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው፣ አስተዳዳሪው፥ በአዳማ ከተማ ስብሰባ ተሳትፈው ከተመለሱ በኋላ፣ እሑድ ምሽት 3፡00 አካባቢ፣ ኢሉ ወረዳ፣ አስጎሪ ከተማ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው፣ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች እንደተወሰዱ አመልክቷል።

ባለፈው ማክሰኞ፣ ሰኔ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ደግሞ መገደላቸውን ጠቁሟል።

የደቡብ ምስራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ ታዬ ጉዲሳ፣ ባሰፈሩት የኀዘን መግለጫ፣ “አቶ በቀለ፣ ጠላት በፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ተገድለዋል፤” ብለዋል።

“ጠላት” በማለት የጠቀሱትን አካል ማንነት ግን በስም ለይተው አልገለጹም።

ሟቹ አስተዳዳሪ፣ “የሕዝቡን ጥቅም ለማስከበር ቁርጠኛ የኾኑና ከራስ ወዳድነት ነፃ የኾኑ መሪ” ነበሩ፤ በማለትም አክለዋል አቶ ታዬ።

የአቶ በቀለ ቃቻ የቀብር ሥነ ሥርዐት፣ በዛሬው ዕለት መፈጸሙን፣ የሰዴን ሶዶ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

በአስተዳዳሪው ግድያ ዙሪያ፣ ከሰዴን ሶዶ ወረዳ እና ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት፣ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በኦሮሚያ ክልል የዚኽ ዐይነቱ ግድያ ሲፈጸም፣ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በምዕራብ ሸዋ ዞን፣ የኦዳ ባርጋ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አብዲሳ ቀነኒ፣ ባለፈው ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በበካቴ ከተማ፣ በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ፣ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን፣ የዞኑ ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ገልጾ ነበር።

በተመሳሳይ ኹኔታ፣ በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም. የነቀምቴ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ፣ አቶ ደሳለኝ ቦኮንጃ፣ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን፣ የከተማው አስተዳደር መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ባለፈው ማክሰኛ፣ በሰዴን ሶዶ ወረዳ አስተዳዳሪ ላይ የተፈጸመውን ጨምሮ፣ በሌሎችም አካባቢዎች እየተፈጸመ ስላለው ግድያ፣ መረጃ እንዳለው የገለጸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ)፣ በየሥፍራዎቹ ተገኝቶ፣ ስለ ኹኔታው እንዳያጣራ፣ የጸጥታ ኹኔታው ዕንቅፋት እንደኾነበት አስታውቋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች፣ በንጹሐን ዜጎች ላይ ስለሚፈጸሙ ግድያዎችም እንደዚኹ፣ መረጃ ቢደርሰውም፣ ባለው የጸጥታ ኹኔታ ምክንያት፣ በቦታው ተገኝቶ ለማጣራት አስቸጋሪ እንደኾነበት፣ ኮሚሽኑ ገልጿል።

መንግሥት፣ ለችግሩ እልባት እንዲሰጥና የሰላማዊ ሰዎችን ግድያ እና መፈናቀል፣ እንዲሁም ንብረት መውደም እንዲያስቆም፣ በተደጋጋሚ እያሳሰበ መቆየቱንም፣ ኢሰመኮ አውስቷል።

XS
SM
MD
LG