በኦሮሚያ ክልል ዛሬም ውጥረትና ግድያ መፈፀሙን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎችና የአንድ ከተማ ከንቲባ ገልፀውልናል። አርብ ከሰዓት ከፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ በኋላ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ወጣቶች ተቃውሞአቸውን ለመግለፅ ዋና የመኪና መንገዶችን በድንጋይ ሲዘጉ እንደነበር ገለልፀዋል።
ይህንንም ተከትሎ የታጠቁ የፀጥታ ኃይሎች ወሰዱት በተባለው እርምጃ የሰው ሕይወት መጥፋቱንና በጥይትና በድብደባ የቆሰሉ ሰዎች እንዳሉም ተናግረዋል። በተለይ በጉደር የሚገኙ አንድ እናት መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የታጠቁ ሰዎች ገብተው ባለቤታቸውን እንደገድሉባቸው ልጃቸውን ደግሞ እንዳቆሰሉባቸው ገልፀዋል።
የክልሉ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋም ሆነ የፌደራል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የእጅ ስልክ ላይ ለተከታታይ ቀናት ባደረግነው የስልክ ሙከራ ስልካቸውን ስለማያነሱ ልናገኛቸው አልቻልንም።
የወረዳና የዞን አስተዳዳሪዎች በበኩላቸው ጉዳዩ ከእነርሱ ቁጥጥር ስር እንዳይደለ ገልፀው ኮማንድ ፖስቱን እንድናነጋግር ገልፀውልናል።
የመከላከያ ሚኒስትር እና የኮማንድ ፖስቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ሲራጅ ፈጌሳና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጌታቸው አምባዬና የእጅ ስልክ ላይ ደውለን ነበር እነርሱም አይመልሱም።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በክልሉ እየተፈፀመ ነው ስለተባለው የመብት ጥሰት በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲን ለማነጋገር ሞከረን ስልካቸው ስለማይነሳ ልናገኛቸው አልቻልንም።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ