በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኦሮሚያ በሙስና ተጠርጥረው የታሰሩት የመንግስት ባለስልጣናት ከ50 እንደማይበልጡ ጸረ-ሙስና አስታወቀ


የኦሮሚያ ክልል የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን በሙስና ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ባለስልጣናት ከሀምሳ የማይበልጡ መሆኑን አስታወቀ።

ይሄ ቁጥር ባለፉት ስድርት ወራት የታሰሩትን እንደማያካትት የክልሉ የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ጠይብ አባ ፎጊ ገልጸዋል።

ከአንድ ሳምንት በላይ የፈጀው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ግምገማ ከ120 በላይ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ባለስልጣናትን የሙስና ጉዳይ መመርመሩን ምንጮችን ጠቅሶ የሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

አቶ ጠይብ እንደሚሉት ቁጥሩ የተጋነነ ነው። ሆኖም ባለፉት ስድስት ወራት ከ1-10 በሚደርስ ጽኑ እስራት የተቀጡት ባለስልጣናት ሲታከሉበት ቁጥሩ ወደዚያው የሚጠጋ ይሆናል።

በተለይ በሰበታ፣ አለምገና፣ ሻሸመኔ፣ ነቀምቴና በጠቅላላው በአዲስ አበባና በአካባቢዋ የሚገኙ ከተሞች ሹማምንት በሙስና ተጠርጥረው ከታሰሩት የሚበዙት ናቸው።

ከህዝብን መሬት ለባላሃብቶችና ለግለሰቦች፤ በጥቅም በመደለል የሚዘርፉ ባለስልጣናት መበራከታቸውን ጠንቅቀው እንደሚያውቁ፤ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሳምንቱ መጨረሻ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል።

“መሬት የዘረፉም ያልዘረፉም ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን። ዋናው አደጋ ዘራፊው ሳይሆን አዘራፊው ነው” ብልዋል አቶ መለስ። መሬት ከዘረፉት ባለሃብቶች ጥቂቶቹ ለፍርድ እንደሚቀርቡና የተቀሩት ደግሞ ምህረት ተደርጎላቸው በከባድ አስተዳድራዊ ቅጣት ይቅርታ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።

“ያዘረፉት የመንግስት ሰራተኖች በሙሉ ግን፤ በሙሉ ፍርድ ቤት ይሄዳሉ። ትልቁ አደጋ የመንግስት ሙስና ነው።” ብለዋል አቶ መለስ።

የኦሮሚያው የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ጠይብ እንደሚሉት፤ በክልሉ ሙስናን ለመከላከልና ተጠያቂነት እንዲኖር መንግስት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ ነው። ሆኖም ሙስናን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጥፋት በጣም ከባድ እንደሆነ አቶ ጠይብ ያሳስባሉ።

ሙስና በኦሮሚያ ክልል ስር የሰደደ እንደሆነና፤ በተለይ ከመሬት ጋር የተያያዘ ስርቆት መበራከቱን ነዋሪዎችም፤ ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለስልጣናትም በተለያየ ጊዜ ይገልጻሉ።

ችግሩን ከስር መሰረቱ ለመቅረፍ ግን፤ ከላይ እስከታች ያለውን መዋቅር መፈተሽ እንደሚያስፈልግ ለአሜሪካ ድምጽ አስተያየታቸውን የሰጡ የአዳማ ነዋሪ ያሰምሩበታል።

XS
SM
MD
LG