እሳቱን የሚያዛምት ነፋስ ሊኖር እንደሚችል ባለሞያዎች አስጠንቅቀዋል
ደቡባዊ ካልፎርኒያ ሎስ አንጀለስ አካባቢ ለቀናት የቀጠለውን ሰደድ እሳት ለማጥፋት የእሳት አደጋ ሠራተኞች ዛሬም መረባረባቸውን ቀጥለዋል፡፡ በቃጠሎው እስካሁን ቢያንስ ሃያ አምስት ሰዎች የሞቱ ሲሆን ኅይለኛ ንፋስና ደረቅ የአካባቢው ሁኔታ ቃጠሎውን ይበልጡን ያስፋፋዋል የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡
ትላንት ማክሰኞ ቀን ላይ ንፋሱ ከተጠበቀው ጥቂት ረገብ ማለቱን ተከትሎ የብሔራዊ የአየር ሁኔታ ክትትል አገልግሎት ዛሬ ረቡዕ ከጠዋት ያነሳ ከቀትር በኋላም ጭምር የነፋሱ ፍጥነት ሊጨምር እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር፡፡
የኢሌክትሪክ ኃይል ኩባኒያዎችም የኤሌክትሪክ መሥመሮች ላይ አዲስ ቃጠሎ እንዳይነሳ ለመከላከል በሚል ከ77 ሺህ የሚበልጡ መኖሪያ ቤቶችን የኤሌክትሪክ ኅይል አቋርጧል፡፡
የእሳት አደጋ ሠራተኞች ካለፈው ሳምንት አንስተው ሁለቱን ዋና ዋናዎቹ ሰደድ እሳቶች እና ሰኞ ዕለት የተነሳውን ቃጠሎ ለመቆጣጠር ባደረጉት ጥረት ያገኙትን ውጤት ነፋሱ መልሶ እንዳይቀለብሰው አስግቷል፡፡
የካልፎርኒያ የደን ጥበቃ እና የእሳት አደጋ መከላከያ መሥሪያ ቤት (ካልፋየር) የምዕራባዊ ሎስ አንጀለሱ ሰደድ እሳት 96 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው አካባቢ ማውደሙን ገልጿል፡፡ እስከ ዛሬ ረቡዕ ማለዳ ድረስ ከሚዛመተው እሳት 18 ከመቶ የሚሆነውን ለመቆጣጠር እንደተቻለም አመልክቷል፡፡
ለ88 ሺህ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲወጡ የተሰጠው ትዕዛዝ አሁንም እንደጸና ሲሆን ሌሎች ወደ 85 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎችም እንዲወጡ ሊታዘዙ እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የሎስ አንጀለስ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ሮበርት ሉና ሰዎች ማስጠንቀቂያውን ከሰሙ ትዕዛዝ እስኪሰታቸው ሳይጠብቁ ቢወጡ ይመከራሉ ብለዋል፡፡ ትዕዛዙን ከሰሙ በኋላ ሳይወጡ የቀሩ ሰዎችን ፖሊሶች ማውጣታቸውን አክለው ተናግረዋል፡፡ የሰደድ እሳቱን ተከትሎ አሁንም የደረሱበት ያልተገኘ ሰላሳ የሚሆኑ ሰዎች መኖራቸውን ባልስልጣናቱ ገልጸዋል፡፡ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት አንዳላቸውም ጠቅሰዋል፡፡
ከዚኹ ጋራ በተያያዘ ማክሰኞ ዕለት አደጋው በተነሳበት አካባቢ ነበሩ የተባሉ ኢትዮጵያዊ አነጋግረናል። ጽዮን ግርማ ነች ያነጋገረቻቸው።
መድረክ / ፎረም