በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኦብነግ ገላልሼ ከተማን ለቅቄ ወጣሁ አለ፣ ነዋሪዎች ቀድሞውንም አልተቆጣጠረም ብለዋል


ባለፈው ሳምንት ሀሙስ በሶማሊ ክልል የሚንቀሳቀሰው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) በገላልሼ ከተማ አካባቢ ባደረገው ጥቃት በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጉዳት ማድረሱንና እስረኞችን ማስፈታቱን አስታውቆ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ አማጺያኑ ለጥቃት ሲዘጋጁ በአካባቢው የፖሊስ ሃይልና ሚሊሻ የደፈጣ ጥቃት ደርሶባቸው 80 የሚሆኑ አማጺያንና፣ ሶስት የፖሊስ ባልደረቦች ሲገደሉ፤ አራት የመንግስት ሀይሎች ቆስለዋል ብሏል።

በዛሬውለት ኦብነግ እንዳስታወቀው ገላልሼ ከተማን ለቆ ወጥቷል። የኢትዮጵያ መንግስት በሄሊኮፕተር የታገዘ ዘመቻ እያካሄደ እንደሆነ ነው ኦብነግ ያስታወቀው።

በሀሙሱ ጥቃት በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጉዳት ከማድረሱ አልፎ በመቶዎች የተቆጠሩ እስረኞችን ማስፈታቱን ይናገራል።

በዚህ ግጭት ከሳምንታት በፊት ደብዛቸው ጠፍቶ የነበረው የአለም ምግብ ድርጅት WFP ሰራተኞች በኢትዮጵያ መንግስት ታስረው ማግኘታቸውንና አሁን በኦብነግ እጅ እንዳሉ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት አማጺያኑ ይዘዋቸዋል የሚለውን የWFP ሰራተኞች ለማስለቀቅ ልዩ ሃሉን ማሰማራቱን የመንግስቱ ቃል አቀባይ አቶ ሽመልስ ከማል አርብለት መግለጻቸው ይታወሳል።

ከአለም የምግብ ድርጅት ባገኘንው መረጃ መሰረት የታገቱት ሰራተኞቹ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።

“ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ስማቸውን ልገልጽ አልችልም፤ ልናገር የምችለው በጂጂጋ የሚገኘው የመስክ ቢሮአችን የሚሰራ አንድ ሾፌርና አንድ የምግብ እርዳታ አሰጣጥ ተቆጣጣሪ ናቸው” ብለዋል የአለም የምግብ ድርጅት ቃል አቀባይ ጁዲዝ ሹለር።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሰራር የታገቱ ሰዎችን ማንነትና ዝርዝር መረጃን የመስጠት ልማድ ባለመኖሩ ተጨማሪ መረጃ መስጠት እንደማይችሉ ሹለር ይናገራሉ።

የአማጺው ሃይል ኦብነግ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር ተነጋግሮ ታጋቾቹን በአለም አቀፍ ቀይ መስቀል አማካኝነት ነጻ ለመልቀቅ እንደሚፈልግ አስታውቋል። በዚህ ላይ የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል። WFP ከታጋቾቹ ቤተሰቦች ጋር በቅርበት እንደሚነጋገር ጁዲት ሹለር ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ የኦጋዴን ህሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር ቃል አቀባይ አቶ ሃሰን አብዱላሂን አነጋግረናል። ዝርዝሩን ከሬድዮ ዘገባው ያዳምጡ።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG