በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ስለኦብነጉ አመራር አባል ተይዞ መሰጠት ከሞቃዲሾ መግለጫ ወጣ


የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባር - ኦብነግ አመራር አባል የሆኑን አብዲከሪም ሼክ ሙሴን በቅርቡ ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳልፎ የሰጠው "ከሃገሪቱ ውስጥ የፀጥታ ሥጋትን ለማስወገድ ባደረገው እንቅስቃሴ የተወሰደ ሕጋዊ እርምጃ ነው" ሲል የሶማሊያ መንግሥት አስታውቋል።

የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባር - ኦብነግ አመራር አባል የሆኑን አብዲከሪም ሼክ ሙሴን በቅርቡ ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳልፎ የሰጠው "ከሃገሪቱ ውስጥ የፀጥታ ሥጋትን ለማስወገድ ባደረገው እንቅስቃሴ የተወሰደ ሕጋዊ እርምጃ ነው" ሲል የሶማሊያ መንግሥት አስታውቋል።

ኦብነግ እርምጃውን በድጋሚ አውግዞ ውንጀላውንም ውድቅ አድርጓል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ መንግሥት ቢያንስ አንድ መቶ የሶማሊያ እሥረኞችን ልትፈታ እንደሆነ ምንጮች መጠቆማቸው ተነግሯል።

ቀልቢ ዻጋ በሚልም ተቀጥያ ስም የሚጠሩትን የኦብነግ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሶማሊያ መንግሥት አሥሮ ለኢትዮጵያ አሣልፎ መስጠቱ ሶማሊያ ውስጥ የሰፋ ተቃውሞ አስነስቶ እንደነበረ ተነግሯል።

ከየአካባቢው ይነሣ የነበረው ቁጣ በማኅበራዊ መገኛዎች ሳይቀር ተሠራጭቶ በመንግሥቱና በሶማሊያ ብሄረተኛ ፖለቲከኞች መካከል ክፍተት ፈጥሮ ታይቷል።

በዚህ ምክንያት ስለጉዳዩ መግለጫ ከመስጠት አፈግፍጎ የቆየው የሶማሊያ መንግሥት የካቢኔውን አስቸኳይ ስብሰባ ትናንት ሞቃዲሾ ላይ ጠርቶ ካካሄደ በኋላ ባወጣው መግለጫ አብዲከሪም ሼህ ሙሴን አሳልፎ የሰጠው ከኢትዮጵያ ጋር የዛሬ ሁለት ዓመት በተፈረመ ስምምነት መሠረት መሆኑን አሳውቋል።

የሁለቱ መንግሥታት የያኔ ስምምነት አልሻባብና ኦብነግ የሽብር ቡድኖች መሆናቸውንና የሁለቱንም ሃገሮች ፀጥታ የሚያናጉ ስለመሆናቸውም የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን የሚደነግግ እንደሆነ መግለጫው አመልክቷል።

ሞቃዲሾ ላይ መግለጫ የሰጡት የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አብዲራህማን ኦማር ኦስማን የካቢኔውን ስብሰባ መግለጫ በንባብ ሲያሰሙ “ግለሰቡ የሶማሊያን ፀጥታ በሚያናጉ አድራጎቶች ላይ የተሠማራና ከሽብሩ ቡድን አልሻባብ ጋር ግንኙነት ያለው የኦብነግ አባል ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያና ሶማሊያ የፀጥታና የምጣኔኃብት ትብብር ስምምነቶች ያሏቸው መሆኑን ያመለከቱት የሶማሊያው የማስታወቂያ ሚኒስትር ቀልቢ ዻጋን አሳልፎ መስጠቱ የሕግ ድጋፍ ያለው እንደሆነ አክለው ተናግረዋል።

ይህንን የሶማሊያ ካቢኔ መግለጫ አስመልክቶ የኦብነግ ቃል አቀባይ አብዱልከድር ሃሰን ሂርሞጌ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ኦብነግ የሽብር ቡድን አለመሆኑን፣ በብዙ የአውሮፓ፣ የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ ሃገሮች ቢሮ ያለው መሆኑንና ኦብነግን ሽብርተኛ ብላ የምትጠራ ብቸኛ ሃገር ኢትዮጵያ መሆኗን አመልክተዋል። በድርጅታቸው ላይ የሚሠነዘሩት ውንጀላዎች “መሠረት የሌላቸው ናቸው” ብለዋል።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

ስለኦብነጉ አመራር አባል ተይዞ መሰጠት ከሞቃዲሾ መግለጫ ወጣ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:34 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG