ዋሺንግተን ዲሲ —
የናይጄሪያ ወታደሮች ትናንት ሌሊት የፖሊሶች የጭካኔ ተግባርን ይቃወሙ በነበሩት ሰለፈኞች ላይ፣ ተኩስ ከፍተዋል የሚለውን ክስ፣ የሃገሪቱ ባለሥልጣኖች እየመረመሩ መሆናቸው ተዘግቧል።
ድርጊቱ የተፈጸመው የሃገሪቱ ትልቋ ከተማና የንግድ ማዕከል በሆነችው ሌጎስ በሚገኘው፣ ሌኪ ቶል ፕላዛ በተባለው መንደር መሆኑ ተገልጿል። አንድ እማኝ ለዜና አውታሮች በገለጸው መሰረት፣ ወታደሮች በቦታው ደርሰው፣ መብራቱ እንደጠፋ ተኩስ ከፈቱ።
አኪንቦሶላ ኦጉንሳንያና ሌሎች የዐይን ምስክሮች፣ በተኩሱ የቆሰሉና የሞቱ ሰዎች እንዳሉ ገልጸዋል።
የተኩሱ ወሬ የተሰማው፣ የሌጎስ ከተማ አስተዳዳሪ ባባጂዴ ሳንዎ ኦሉ፣ የ24 ሰዓታት የሰዓት እላፊ ገደብ ባወጁበት፣ የመጀመሪያ ሌሊት ነወ። የሰዓት ዕላፊው ገደብ ከምሽቱ 10 ሰዓት አንስቶ፣ በሥራ ገብታቸው የመገኘት ግዴታ ያለባቸው ሰራተኞች ካልሆኑ በስተቀር፣ ማንም እንዳይንቀሳቀስ ያዛል።
የሌጎስ ክፍለ-ግዛት አስተዳደር በጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ማዘዙን፣ የአስተዳዳሪው ቃል አቀባይ፣ ግቦየጋ አኮሲ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ፣ ሌኪ ቶል ፕላዛ ላይ በተከፈተው ተኩስ፣ የሞቱ ሰዎች እንዳሉ፣ ተአማኒ ማስረጃ ማሳየቱን ገልጿል።