ለጋዛው ጦርነት ከተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ፣ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ሲካሄድ የነበረው ድርድር ያሳደረው ተስፋ መመናመን እና ሜክሲኮ ለዓለም ገበያ በምታቀርበው ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት መጠን ላይ ተጨማሪ ቅነሳ ለማድረግ የያዘችውን እቅድ ተከትሎ በዛሬው ዕለት የዓለም የነዳጅ ዋጋ መናሩ ተዘግቧል።
ትናንት ሰኞ ካይሮ ላይ የተካሄደውን አዲስ ዙር የተኩስ አቁም ድርድር ተከትሎ በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ የማሽቆልቆል አዝማሚያ ማሳየት ቢጀምርም፤ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፣ ጦራቸው በጋዛዋ የራፋህ ግዛት ጥቃት የሚፈከፍትበት ‘ቀን ተቆርጧል’ ካሉ በኋላ፣ የአካባቢው ውጥረት ‘ይረግባል’ በሚል አሳድሮት የነበረውን ተስፋ እያመከነ መሆኑን ተንታኞች ተናግረዋል።
የግጭቱ አለማብቃት ሌሎች አገሮችንም ወደ ጦርነት እንዳይስብ፤ በተለይም ደግሞ ዋናዋ የሃማስ ደጋፊ እና በዓለሙ የነዳጅ አምራች አገሮች ድርጅት፣ ለዓለም ገበያ በሚቀርበው የነዳጅ መጠን በሦስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘውን ኢራንን ወደ ጦርነቱ እንዳያስገባ ያሳደረው ሥጋት እንዲቀጥል ማድረጉ ተዘግቧል።
በተጨማሪም የሜክስኮው መንግስታዊ የነዳጅ ኩባንያ ‘ፔሜክስ’ በቀኑ ለዓለም ገበያ ከሚያቀርበው 330ሺሕ በርሜል መጠን ያለው ነዳጅ በመቀነስ ተጨማሪ ነዳጅ ለአገር ውስጥ ማጣሪያዎች ለማቅረብ የያዘው ዕቅድ አሳሳቢውን ሁኔታ ይበልጥ እንዳባባሰውም ተመልክቷል። ውሳኔውም ኩባንያው ለዩናይትድ ስቴትስ፣ ለአውሮፓ እና ለእስያ ተቀባዮቹ ያቀርብ የነበረውን ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት መጠን በአንድ ሶስተኛ ይቀንሰዋል ተብሏል።
ፔሜክስ አዲሱን ውሳኔውን ይፋ ከማድረጉ አስቀድሞም በያዝነው የሚያዝያ ወር ውስጥ በየቀኑ ከሚያቀርበው የነዳጅ ዘይት መጠን በ436ሺሕ በርሜል ቀንሶ ነበር።
መድረክ / ፎረም