ዩክሬን ባለፈው ሳምንት፣ 37 ካሬ ኪሎሜትር የሚሸፍነውን ምስራቃዊ እና ደቡባዊ የዩክሬን ግዛት መልሳ መያዟን አስታወቀች።
የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ሀና ማሊአር በቴሌግራም ባስተላለፉት መልዕክት፣ የዩክሬን ወታደሮች በስተምስራቅ ወደሚገኘው ባክሙት እየገፉ መሆኑን እና፣ ሩሲያ፣ ሊማን፣ አድቪየካ እና ማሪንካ በተባሉት አካባቢዎች በኩል እያጠቃች መሆኑን ገልፀዋል።
ማሊየር አክለው በተጠቀሱት አካባቢዎች ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ዩክሬን ያገኘቻቸው ድሎች አብዛኞቹ በስተደቡብ ባሉት አካባቢዎች መሆኑን ያስረዱት ማሊየር፣ የዩክሬን ጦር በማሊቶፖል እና በርዲያስካ አካባቢዎች ጥቃት ማካሄዳቸውን ጨምረው አብራርተዋል።
ዩክሬን ጦርነቱ ከጀመረ እ.አ.አ 2022 ወዲህ በሩሲያ የተያዙባትን ግዛቶች ለማስመለስ ማጥቃት የጀመረችው በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር።
የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው የሩሲያ የደህንነት አገልግሎት መግለጫን ጠቅሰው እንደዘገቡት ሩሲያ የክራይሚያ ባህረገብ ሀላፊ አድርጋ በሾመችው ግለሰብ ላይ የተቃጣ የግድያ ሙከራ አክሽፋለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለተኛ ዓመቱን ሊያስቆጥር በተቃረበው የዩክሬን ጦርነት የሩሲያን ጥቃት የሚቃወመውን ዓለም አቀፍ ጥምረት ለማጠናከር የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ አውሮፓ ተጉዘው ሶስት ሀገራትን ይጎበኛሉ።
ባይደን በሚቀጥለው ሳምንት ለአምስት ቀናት በሚያደርጉት ጉዞ ዋና ትኩረታቸው በሐምሌ አራት እና አምስት፣ በሊትዌንያ ዋና ከተማ ቪልኒየስ የሚካሄደው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ስብሰባ ይሆናል።