ሰሞኑን በአዲሰ አበባ ከተማ ለአራት ቀናት የቆየ ውይይት ያካሄዱት ተቃዋሚዎቹ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሁሉን አካታች የኦሮሚያ ክልል የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
“ሐሳቡ የቀረበው ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ሰላም ለማምጣት የጋራ መንግሥት ስለ ሚያሰፈልግ ነው” ሲሉ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል።
“የኢትዮጵያ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ መሠረት በምርጫ የተቋቋመ ነው” ያሉት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቃል አቀባይ ኃይሉ አዱኛ በበኩላቸው፣ የፓርቲዎቹ መግለጫ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው” ሲሉ ለአሜሪካ ድምፅ ምላሽ ሰጥተዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ባወጣው መግለጫ፣ በኦነግና በኦፌኮ የተጠራውን ጉባኤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋራ አብሮ የሚሄድ ፕሮጀክት ነው በማለት አውግዟል።
ተቃዋሚዎቹ የኦሮሞ ነጻነት ግንቀባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ለአራት ቀናት በተካሄደው ጉባኤ ላይ ለግጭት መነሻ የሚኾኑ የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ ችግሮችንም አንስተው መነጋገራቸውን የኦፌኮ ሊቀመንበር ተናግረዋል።
ይሄንኑ መነሻ አድርገው መግለጫ ያወጡት የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባርና ሌሎች በሶማሌ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ተቃውሞ አቅርበዋል።
ኦፌኮና ኦነግ፣ ድሬዳዋ እና ሞያሌን ጨምሮ በአንዳንድ ግዛቶች ላይ ይገባኛል ጥያቄ ማንሳታቸውን የጠቀሱት ፓርቲዎቹ፣ አካሔዱ የፌዴራል ሕገ መንግሥቱን እና በተለያዩ ብሔረሰቦች መካከል ያለውን በሰላም አብሮ የመኖር መርህ ይፃረራል በማለት አውግዘዋል።
በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ሐሳባቸው ጥያቄዎች በድርድርና በንግግር እንዲፈቱ ማድረግ መሆኑን አብራርተዋል። ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
መድረክ / ፎረም