- ኦቻ ግድያውን አውግዟል
ግጭት በሚካሄድበት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ዳውንት ወረዳ ውስጥ ያሬድ መለሰ የተባሉ የረድኤት ሠራተኛ ለቤዛ ክፍያ ታግተው መገደላቸውን እንደሚያወግዝ በተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ዛሬ ለቪኦኤ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ማስተባበሪያ ቢሮው “ያልታወቁ ወንጀለኛ ታጣቂ ቡድኖች” ሲል በገለጻቸው ቡድኖች ግለሰቡ መገደላቸውን መግለጫው አመልክቷል።
አቶ ያሬድ መለሰ በእንግሊዝኛ የምሕጻር ስሙ ASDEPO የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የማኅበራዊ ዕድገትና የአካባቢ ጥበቃ ድርጅት የሥነ ምግብ ባለሞያ እንደነበሩ መግለጫው አመልክቷል።
“አቶ ያሬድ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም የሰብአዊ ሥራቸውን በትጋት ሲሠሩ ነበር” ያሉት የማስተባበሪያ ቢሮው የኢትዮጵያ ኃላፊ ዶ/ር ራሚዝ አላክባሮቭ “ማንኛውም ጥቃት፣ ማስፈራሪያ፣ ዝርፊያና ቤዛ ጥየቃ ተቀባይነት የሌለውና መተዳደሪያ ደንባቸውን የሚጥሱ ናቸው” ሲሉ አክለዋል።
መግለጫው የሰብአዊ መብት ሠራተኛው ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ታግተው ነሐሴ 3 ቀን መገደላቸው ይፋ መውጣቱ ኦቻ ለቪኦኤ በኢሜል ገልጿል።
አቶ ያሬድ መለሰ ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ዓመት የተገደሉ ስምንተኛ የረድኤት ሠራተኛ መሆናቸው እና ስድስቱ የተገደሉት አማራ ክልል ውስጥ መሆኑን መግለጫው አክሎ አመልክቷል፡፡ ቢያንስ 14 የረድኤት ሠራተኞች ላይ ጠለፋ መፈጸሙን የሚገልጹ ሪፖርቶች መውጣታቸውን አውስቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የተሰኘው አካል በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፣ በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ሌሎች ክልሎች በሰብአዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መበራከቱን ከተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሪፖርቶች እንደደረሱት ጠቅሶ፣ ግጭት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ የሰብአዊ ድጋፍ ሠራተኞች ደህንነት እንዲጠበቅ ጠይቋል።
ስለጉዳዩ በፊዴራሉ መንግሥትም ይሁን በአማራ ክልል ባለሥልጣናት ለጊዜው የተሰጠ አስተያየት የለም፡፡ የአቶ ያሬድ መለሰን ጠለፋና ግድያ በሚመለከት በቀረቡት ግልጽ ያልሆኑ ሪፖርቶች ዙሪያ የአሜሪካ ድምጽ ለጊዜው ከገለልተኛ ምንጭ ማረጋገጫ አላገኘም፡፡
መድረክ / ፎረም